ግንቦት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ወኪላችን እንደገለጸው፣ ክልሉን በሚያስተዳድሩት በኦህዴድና በሃረር ብሄራዊ ሊግ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረው ውጥረት በሃረር ከተማ ዙሪያ ከተገኑበት ቤቶች ጋር የተያያዘ ነው።
የክልሉ መንግስት ከ2003 ዓም በሁዋላ በህገወጥ መንገድ ተገንብተዋል ያላቸውን ቤቶች ለማፍረስ እንቅስቃሴ ቢጀምርም፣ከህዝቡ በደረሰበት ተቃውሞ ምክንያት ያሰበው ሳይሳከለት ቀርቷል። በአፍራሽ ግብረሃይልና በፖሊስ የተጋዘው ቤት የማፍረስ እንቅስቃሴ ሊሳካ አለመቻሉን ተከትሎ የምስራቅ እዝ ጣልቃ ገብቶ በህዝቡ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ቢጠየቅም፣ የምስራቅ እዝ ከክልሉ መንግስት ጋር ባለው የቆዬ ቅራኔ ጣልቃ ለመግባት ፈቃደኛ አልሆነም።
በመልካም አስተዳደር ስም ኦህዴድ ጠንካራ አባሎቼ እንዲገመገሙና እንዲታሰሩ አድርጎብኛል በሚል ቅሬታ የሚያሰማው ሃብሊ ፣ የኦሮሞ አርሶአደሮች በሚበዙበት በድሬ ጥያራ ህገወጥ ቤቶችን ለማፍረስ የተደረገውን እንቅስቃሴ የአካባቢውን ሰዎች የተለያዩ መሳሪያዎችን በማስታጠቅ ተቃውሞ እንዲያነሱ ያስደረገው ኦህዴድ ነው በማለት ክስ ማሰማት ጀምሯል። የድሬ ጥያራ ወረዳ አስተዳዳሪና የኦህዴድ አባሉ አቶ አብደላ መንን ቅዳሜ ሚያዚያ 28 ከ500 በላይ ሰዎችን በስብሰባ ጠርተው፣ “ የመረጣችሁኝ እናንተ ናችሁ፣ ከዚህ በሁዋላ ከእናንተ ጋር ሆኜ ቤታችሁ እንዳይፈርስ እታገላለሁ፣ የሸንኮር ወረዳ ምንም አይመለከተውም፣ እናንተ በእኛ ስር ናችሁ “ በማለት መናገራቸው ህዝቡን ቢያስደስትም፣ የክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ ሙራድ አብዱላሀንና የሃብሊ አመራሮችን አስቆጥቷል።
የሁለቱ ፓርቲዎች ውዝግብ ወዴት እንደሚያመራ ለመገመት ባይቻልም፣ ህዳር 29 በሃረር በሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች በአል ዝግጅት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በሃረሪ ክልል ባለው የስልጣን ክፍፍል ሀብሊ የፕሬዚዳንቱን፣ ኦህዴድ የምክትል ፕሬዚዳንቱን ቦታ የያዙ ቢሆንም፣ በክልሉ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆችና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአማራ ተወላጆች በአስተዳደሩ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ አላቸው። የሌሎች ብሄረሰብ አባሎች በክልሉ የተነሰራፋውን ግልጽ ዘረኝነት ቢቃወሙም መፍትሄ የሚሰጣቸው ማጣታቸውን በተደጋጋሚ ይናገራሉ።