ኢሳት (ጥር 3 ፥ 2008)
ሰኞ ሃረማያ ዩንቨርስቲ ዳግም የተቀሰቀሰውን የተማሪዎችን ተቃውሞ ተከትሎ ዩንቨርስቲው ትምህርት ማቋረጡን እማኞች ገለጡ።
የጸጥታ ሃይሎች በተማሪዎች ላይ እየወሰዱ ባለው የሃይል እርምጃ በርካታ ተማሪዎች መደብደባቸውንና ቁጥራቸው ሊታወቅ ያልቻለ ተማሪዎች ለእስር መዳረጋቸው ታውቋል።
ከዚህ በፊት ለእስር የተዳረጉ ተማሪዎች እንዲፈቱ ጥያቄን ማቅረብ የጀመሩ በርካታ ተማሪዎች የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱትን የሃይል እርምጃ እንዲቆም ጥያቄ ማቅረባቸው ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ይሁንና ተማሪዎቹ ጥያቄን ማቅረብ በጀመሩ ጊዜ በቅርብ ርቀት የሰፈሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ወደ ዩንቨርስቲ ቅጥር ግቢ በመግባት እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን ተማሪዎች ገልጸዋል።
የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ በርካታ ተማሪዎች ክፉና የተደበደቡ ሲሆን ወደ ህክምና ተቋማት የተወሰዱ እንዳሉም ተገልጿል።
ሰኞ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ማክሰኞ በአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፎ ተባብሶ መቀጠሉንና ነዋሪዎች የጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱትን የሃይል እርምጃ ማውገዛቸውንም እማኞች ለኢሳት አስረድተዋል።
በአካባቢው የሚኖረው አርሶ-አደር ገበሬም ተቃውሞውን እንደተቀላቀለ ታውቋል። የፌዴራል ፖሊስ አባላት የተኩስ እርምጃ ምላሽን በመስጠት በነዋሪዎች ላይ ክፉኛ ጉዳት እንዳደረሱ የተለያዩ አካላት አስታውቀዋል።
የሃረማያ ዩንቨርስቲ ሙሉ በሙሉ ትምህር ማቋረጡን የተናገሩት ተማሪዎች የአካባቢው ነዋሪዎች በተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ድርጊት በማውገዝ ተቃውሞ ማሰማት መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
ሁለተኛ ወሩን ይዞ የሚገኘው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ማክሰኞ ከሃረማያ አካባቢ በተጨማሪ በምስራቅና በምዕራብ ወለጋ በሚገኙ አካባቢዎች በአዲስ መልክ መቀጠሉንም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ዳግም የተቀሰቀሰውን የተማሪዎች ተቃውሞ ተከትሎም ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሃይል በበርካታ ዩንቨርስቲዎች በመሰማራት ላይ መሆኑ ታውቋል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ባለው እርምጃ በትንሹ 140 ሰዎች መገደላቸውን በመግለጽ ተቃውሞ በመቀጠሉ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ አስታውቀዋል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ በትንሹ 5ሺ ሰዎች ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙ በቅርቡ ይፋ ማድረጉም ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ቅዳሜ በጅማ ዩንቨርስቲ በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር 33 መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ጥቃቱን የፈጸመው አካል ማን እንደሆነ አልተገለጸም።
ቅዳሜ ምሽት በጅማ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ላይ በተወረወረው በዚህ የእጅ ቦምብ በተጎዱ 33 ተማሪዎች ውስጥ ሁለቱ ጉዳታቸው የከፋ መሆኑም ተመልክቷል። ተማሪዎቹ በመኖሪያ አካባቢያቸው ተወስነው ተቃውሞ በማሰማት ላይ ሳሉ ቦንቡ መወርወሩን የአይን ምስክሮች ገልጸዋል።
በኦሮሚያ አካባቢ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ እስካሁን በሶስት የተለያዩ ቦታዎች ቦንቦች የተወረወሩ ሲሆን በዲላ ዩንቨርስቲ በተሰነዘረው ጥቃት ተማሪዎች ሲገደሉ በጅማናበአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ ጥቃቶች በርካቶች ቆስለዋል።
ፍንዳታዎቹ በማን እንደተፈጸሙ እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም።