በሃረማያ ዩንቨርስቲ የተጀመረው የተማሪዎች ተቃውሞ በአጎራባች ቀበሌዎች ተዛመተ

ኢሳት (ጥር 4 ፥ 2008)

ሰኞ በሃረማያ ዩንቨርስቲ የተጀመረው የተማሪዎች ተቃውሞ በአካባቢው መዛመቱንና በአካባቢው ውጥረቱ አለመርገቡን ነዋሪዎች ገልጸዋል። የዩንቨርስቲው አስተዳደር ተማሪዎች መደበኛ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ ቢያቀርብም ተማሪዎቹ ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

በምስራቅ ሃረርጌ አካባቢ ባሉ ከተሞች ረቡዕ ተመሳሳይ ተቃውሞ ሲያካሄዱ ያረፈዱ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ከፍተኛ ተቃውሞ በመካሄድ ላይ መሆኑም ታውቋል።

ተቃውሞው በአዲስ መልክ ቀጥሎ በሚገኙባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱት እርምጃም ተጠናክሮ እንደቀጠለና የሟቾቹ ቁጥር እየጨመረ መሆኑንም የተለያዩ አካላት አስታውቀዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የፓርቲ አመራሮች በእስካሁን የጸጥታ ሃይሎች እርምጃ በትንሹ 140 ሰዎች መገደላቸውን ሲገልጹ ቢቆዩም ቁጥሩ ከ150 በላይ መድረሱም ተነግሯል።

በአዳማ ናዝሬት ዩንቨርስቲ እንዲሁም በዲላና አምቦ ዩንቨርስቲዎች ዳግም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በምስራቅ ሃረርጌ ኦሮሚያ ክልሎች በመዛመት ላይ መሆኑን ከሃገር ቤት መረጃ አመልክቷል።