በሃረማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ታሰሩ

በሃረማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ታሰሩ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 21 ቀን 2010 ዓ/ም) የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ትምህርት እንዲጀምሩ በወታደራዊ እዙ ቢታዘዙም፣ ቀሪዎቹ ተማሪዎች ሳይመጡ ትምህርት አንጀምርም በማለታቸው ከየክፍላቸው እየተወሰዱ መታሰራቸውን የአካባቢው ወኪላችን ገልጿል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች ግቢውን ተቆጣጥረው ተማሪዎችን ከክፍላቸው እያወጡ ወደ እስር ቤት ወስደዋቸዋል።
ከሳምንት በፊት ተማሪዎች ምዝገባውን ካካሄዱ በሁዋላ ፣ ከፋሲካ በሁዋላ እንገናኝ በማለት ብዙዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመልሰው ነበር። በግቢው ውስጥ መቆየት የመረጡት ተማሪዎች በበኩላቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው የሄዱ ተማሪዎች ሳይመለሱ ትምህርት አንጀምርም የሚል አቋም ይዘዋል።
የሃረማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ትምህርት እንዲጀምሩ ካስቀመጡዋቸው ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ወታደሮች ከግቢያቸው እንዲወጡ የሚጠይቅ ነው። ይሁን እንጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሰበብ በማድረግ ወታደሮች አሁንም ከግቢያቸው አልወጡም። በዚህ ሁኔታ ሰላም አግኝተው መማር እንደማይችሉ የተረዱት ተማሪዎች፣ ይህና ሌሎችም ጥያቄዎቻቸው እስኪመለሱ ትምህርታቸውን በማቋረጥ መቃወምን መርጠው ነበር። ወታደራዊ አዛዦች ተማሪዎችን ወደ እስር ቤት መውሰዳቸው በግቢው ውስጥ ተጨማሪ አለመረጋጋት ሊፈጥር እንደሚችል የኢሳት ወኪል ትዝብቱን ገልጿል።