በሁለት ጋዜጠኞችና በ18 ተከሳሾች ላይ ከ6 ወር እስከ 5 አመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ማክሰኞ ተላለፈ

ኢሳት (ታህሳስ 25 ፥ 2009)

በቅርቡ የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው ሁለት ጋዜጠኞችና 18 ተከሳሾች ከስድስት ወር እስከ አምስት አመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ማክሰኞ ተላለፈባቸው። ተከሳሾቹ ድምጻችን ይሰማ ሲሉ በችሎቱ መፈክር ማሰማታቸውም ተመልክቷል።

የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 18ቱ ተከሳሾች የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ከእስር ቤት ለማስወጣት የሽብር ጥቃት ለማድረስ በተመሰረተባቸው የሽብር ወንጀል ክስ ባለፈው ሳምንት የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል።

ማክስኞ የፍርድ ውሳኔውን ያስተላለፈው ፍርድ ቤቱ በከድር መሃመድ የሱፍ የክስ መዝገብ ጥፋተኛ በተባሉ 19 ከተሳሾች ላይ የአምስት አመት ከስድስት ወር የእስር ቅጣት ፍርድ መሰጠቱ ታውቋል።

በዚሁ ክስ መዝገብ ውስጥ የሚገኘው ጋዜጠኛ ዳርሴማ ሶሪ ካለበት የሳንባ በሽታ ምክንያት በአራት አመት ከአምስት ወር እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማክሰኞ የፍርድ ውሳኔውን በጽሁፉ ባሰማ ጊዜ ተከሳሾች “ድምጻችን ይሰማ” ሲሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በችሎት ማሰማታቸውንም አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል።

የፍርድ ውሳኔውን ለመስማት በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ በርካታ ሰዎች ተገኝተው የነበረ ሲሆን፣ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተሰባሰቡ ሰዎችን እንደበተኑም ለመረዳት ተችሏል።

የተከሳሾቹ ጠበቃ የሆኑት አቶ ሙስጠፋ ሱሌይማን በበኩላቸው የተላለፈው ፍርድ ተገቢ አለመሆኑንም በመግለጽ ደንበኞቻቸው ህግ በሚፈቅድላቸው መሰረት ሃሳባቸውን በነጻነት ለመግለጽ ባደረጉት ጥረት ለእስር መዳረጋቸው ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

የፍርድ ውሳኔን ከተላለፈባቸው መካከል አራት ተከሳሾች በቅርቡ በቂሊንጦ እስር ቤት ደርሶ በነበረ የእሳት አደጋ ተሳታፊ ናችሁ ተብለው ሌላ ክስ ተመስርቶባቸው ይገኛል።

ከሳሽ አቃቤ ህግ ከሁለት አመት በፊት ተከሳሾቹን በሽብርተኛ ወንጀል መክሰሱ የሚታወስ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የሽብርተኛ ወንጀል ድርጊትን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ሲገለጽ ቆይቷል።

የሙስሊሙ ማህበረሰብ ከአራት አመት በላይ መንግስት በሃይማኖታቸን ጣልቃ ገብቷል ብለው ሲያካሄዱ የነበረውን የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ 18 የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።

የኮሚቴ አባላቱ የእስር ቅጣት ከተላለፈባቸው በኋላ መንግስት ለዘጠኙ ምህረት በማድረግ ከእስር መለቀቁ ይታወሳል።

ይሁንና አሁንም ድረስ በእስር ላይ የሚገኙ የኮሚቴ አባላቱን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች በእስር ላይ መሆናቸውን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።