በሁለት አመታት ብቻ ከ400 ሺ በላይ ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ ተሰደዋል

ጥቅምት ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፉት 2 ዓመታት ብቻ ከ400 ሺ በላይ ዜጎች   ሲሆን፣ በህጋዊ መንገድ የተጓዙትን ሲጨምር አሀዙ በእጥፍ ሊጨምር ይችላል።

መንግስት በቅርቡ ለስራ በሚል ወደ ውጪ በሚጓዙት ላይ እገዳ መጣሉ ይታወቃል።  የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ስምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ አበበ ሀይሌ እንዳሉት ፥ እገዳው ከተጣለባቸው ሀገራት መካከል ሊባኖስ ፣ ኳታር ፣ ሳውዲ አረብያ ፣ ኩየት ፣ የመን ፣ ሱዳንና ደቡብ አፍሪካ ይገኙበታል።

በእገዳው መሰረት ካሁን ቀደም ቪዛ ያገኙትን ጨምሮ ቪዛ ለማግኘት እየተጣጣሩ ያሉትም ቢሆን ወደ ሀገራቱ መጓዝ አይችሉም።፤ እገዳው በቤት ሰራተኝነት ተቀጥሮ ለመስራት ከሚደረጉት ጉዞዎች ባሻገር አለም አቀፋዊ ተቀባይነት ባላቸው ሙያዎች ላይ የሚደረጉ ጉዞዎችን እንደማይመለክትም  ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በመንገድ የቀረው ቀርቶ ወደ መጨረሻ መዳረሻ ሀገር የገቡት ዜጎች እጣ ፈንታ አብዛኛውን ጊዜ ስቃይና እንግልት ቢሆንም ፥ ዛሬም በዚያ የሞት ጎዳና ላይ የሚተሙ ዜጎች ቁጥር ሊቀንስ አልቻለም።

ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር  በሰጠው መግለጫ  እገዳው ከስድስት እስከ ሰባት ወራት ይቆያል።

በአገሪቱ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣው ድህነትና ስራ አጥነት ለስደቱ ዋና ምክንያቶች ናቸው። ከፖለቲካ ጋር በተያያዘም የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር በእየጊዜው እየጨመረ መሄዱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃዎች ያመለክታሉ።