በሀገሪቱ አዲስ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ጥሪ ቀረበ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 16/2010)

በዶክተር መረራ ጉዲና የሚመራው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ በሀገሪቱ አዲስ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ጥሪ አቀረበ።

ፓርቲው ባካሄደው የድርጅቱ 2ኛ ጉባኤ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን ገምግሟል።

ዶክተር መረራና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሁሉም የኦፌኮ አመራሮች ከእስራት እንዲፈቱም ጥሪ አቅርቧል።

የኦህዴድ መሪዎች ለሕዝብ ላሳዩት ወገናዊነትም አድናቆቱን ገልጿል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመጡ አባላቱ ጋር ያካሄደውን የድርጅቱን 2ኛ ጉባኤ በማስመልከት ባለፈው ቅዳሜ ባወጣው ባለ 11 ነጥብ የአቋም መግለጫ ባለፉት 5 አመታት በሀገሪቱ ለቀጠለው ቀውስ የኢሕአዴግ መንግስትን ተጠያቂ አድርጓል።

በዚህም የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ያጠፋ ለፍርድ እንዲቀርብ እንዲሁም ለወደመው ንብረት ካሳ እንዲከፍል ኦፌኮ ጠይቋል።

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ ለሰዎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑት የመከላከያ ሰራዊት፣የፌደራል ፖሊስና የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይልን ጨምሮ እጃቸው ያለበት ሃላፊዎች በሙሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ በመግለጫው ጠይቋል።

የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦሕዴድ/መሪዎች የሕዝብን መብት ለማስከበር በጀመሩት ተግባር እንዲቀጥሉና የኦፌኮንም ሰላማዊ ትግል እንዲያግዙም ጥሪ አቅርቧል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለመብትና ለነጻነት የሚያደርገውን ትግል በመደገፍ ከኦፌኮና መሰል ሰላማዊ ሃይሎች ጋርም እንዲተባበር ጥሪውን ያቀረበው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ አለም አቀፉ ማህበረሰብም ሕዝብ እያለቀ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ዝምታውን እንዲሰብር ጥሪ አቅርቧል።

በኢንቨስትመንት ለተሰማሩ ሃይሎችም ኦፌኮ ባቀረበው ጥሪ በተለይ የውጭ ባለሃብቶች ሶስት አራተኛውን መዋዕለ ንዋያቸውን ባፈሰሱበት ኦሮሚያ ክልል ኢሕአዴግ በሕዝቡ ላይ የሚያደርሰውን ፍጅት እንዲያወግዙም ጠይቋል።

የኦፌኮ ሊቀመንበሩ ዶክተር መረራ ጉዲና፣ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች በወህኒ ቤት እንደሚገኙ የአመራር አባላቱ ከእስር እንዲለቀቁም ጥሪ አቅርቧል።

2ኛው የኦፌኮ ድርጅታዊ ጉባኤ ባካሄደው የአመራር ምርጫ በወህኒ ቤት የሚገኙት መሪዎቹ እንዲሁም ሁሉም የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በነበራቸው ሃላፊነት እንዲቀጥሉም መወሰኑን አስታውቋል።