በሀገረማርያም ጳጳሱ ለአንድ ሰአት ታግተው ተለቀቁ

የካቲት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከአርሴማ ቤተክርስቲያን የውስጥ ችግር ጋር በተያያዘ ከመንግስት ጋር በመሆን የድርጅት ስራ ሰርተዋል ተብለው የተወቀሱት አቡነ ገብርኤል፣ ትናንት ለአንድ ሰአት ያክል ታግተው ተለቀዋል።

ህዝብ በመወከል ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የአገር ሽማግሌዎች ታስረው በህዝብ ግፊት እንዲፈቱ ከተደረገ በሁዋላ፣ ለችግሩ መፍትሄ ያስገኛል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም፣ ችግሩ እልባት ሳያገኝ ቀርቷል። ጳጳሱ በህዝቡ ከታገቱ በሁዋላ በአገር ሽማግሌዎች ማግባባት ሊለቀቁ መቻላቸውን ታስረው ከተፈቱት መካከል አንዱ የሆኑት የቦረና ዞን የአንድነት ፓርቲ አደራጅና የምክር ቤት አባል አቶ ጌታቸው በቀለ ለኢሳት ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው እንደሚሉት መንግስት በጉዳዩ ላይ እጁን በማስገባቱ ችግሩ እንልባት እንዳያገኝ አድርጎታል። 30 የሚሆኑ የአገር ሽማግሌዎች ነገ ማክሰኞ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ለፓትርያርኩ ችግራቸውን እንደሚያሰሙ ለማወቅ ተችሎአል።