በሀድያ ዞን አምቡላንሶች ለምርጫ ቅስቀሳ እየዋሉ በመሆኑ ህመምተኞች በተለይም ነፍሰ ጡር እናቶች ህክምና ሳያገኙ ለሞት እንደሚዳረጉ ነገረ ኢትዮጵያ ዘገበ።

ሚያዝያ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሚያዝያ 20/2007 ዓ.ም አንዲት ምጥ የተያዙ እናት በአቅራቢያቸው በሚገኝ የጎምበራ የጤና ጣቢያ በሄዱበት ወቅት ‹‹ከአቅማችን በላይ ነው!›› ተብለው ወደ ሆሳና ሪፈራል ሆስፒታል ሄደው እንዲታከሙ ሪፈር ቢጻፍላቸውም በትራንስፖርት ችግር ነፍሳቸው ማለፉን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡

ለጎምበራ ጤና ጣቢያ የተመደበችው አምቡላንስ በጎምበራ ወረዳ ኦሌ ቀበሌ ለገዥው ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ በመውጣቷ ቤተሰብ ነፍሰጡሯን ከጎምበራ ጤና ጣቢያ ወደ ሀድያ ሪፈራል ሆስፒታል በቃሬዛ ለመውሰድ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ወደ ሀድያ ሆስፒታል በቶሎ መድረስ ባለመቻላቸው የነፍሰ ጡሯ ህይወት መንገድ ላይ ሊያልፍ ችሏል፡፡ አምቡላንሶች ለምርጫ ቅስቀሳ በመዋላቸው ምክንያት በርካታ ህመምተኞች በተለይም እናቶችና ህፃናት በቶሎ ወደ ሆስፒታል መድረስ ባለመቻላቸው ተመሳሳይ ችግር እየገጠማቸው ነው፡፡