“በሀይማኖት ግጭቶች ውስጥ፤ የመንግስት እጅ አለበት” ተባለ

የካቲት 21 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ኢትዮጵያ ውስጥ በሀይማኖት ምክንያት በሚፈጠሩ ግጭቶች ውስጥ የመንግስት ባለሥልጣናት እጅ አለበት ሲሉ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ይህን ያሉት፤በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትርና በብሮድካስት ባለሥልጣን ትብብር  ለህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ከየካቲት 15 እስከ 17 ድረስ በተሰጠ ሥልጠና ላይ ነው።

በደብረዘይት የ እንሥሳት ጥበቃ ተቋም አዳራሽ ውስጥ በተካሄደው  ሥልጠና  ከተሳታፊዎቹ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል፦”መንግስት ለምን በሀይማኖት ጣልቃ ይገባል?እንዲሁም፤ የ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ገና ባልተፈረደባቸው ተከሳሾች ላይ ‘አኬልዳማ’በሚል ርዕስ  ከሙያዊ ሥነ-ምግባር ውጪ የሆነ ሥራ ሢሰራ፤የብሮድካስ ባለሥልጣን ጉዳዩን ችላ በማለት ሀላፊነቱን አልተወጣም”የሚሉት ይገኙበታል።

በሀይማኖት ጉዳይ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶክተር ሽፈራው፤በሀይማኖት ዙሪያ በሚፈጠሩ ግጭቶች ውስጥ የመንግስት ባለሥልጣናት እጅ እንዳለበትና ከባለስልጣናቱም መካከል ቅጣት የተወሰነባቸው እንዳሉ ተናገረዋል።

ይሁንና፤ቅጣት የተላለፈባቸው ባለሥልጣናት እነማን እንደሆኑ በስም ከመግለፅ ተቆጥበዋል።

ዶክተር ሽፈራው አያይዘውም ፦” በኢትዮጵያ፤ህጋዊውን መንግስት ገልብጦ የሸሪያ መንግስት ለማቋቋም ዕቅድ ነድፎ ከ 30 ዓመታት በላይ ሲንቀሳቀስ የነበረ አክራሪ ቡድን አለ” ሲሉ ተደምጠዋል።

“ይህ ቡድን በውጪ ሀይሎች የገንዘብ ድጋፍ  ፍላጎቱንና እምነቱን በ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ በሀይል በመጫን፣መስጊዶችንና ቤተ-ክርስቲያኖችን በማቃጠልና የሌሎች እምነት ተከታዮችን ጭምር በሀይል በማስለም  የራሱን መንግስት በሀይል ለመመስረት የተደራጀ ነበር”ሲሉም አክለዋል-የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ።

ከእነዚህም ኃይሎች መካከል ለመንግስት ታማኝ በመምሰልና ለሀገር ተቆርቋሪነትን በማንፀባረቅ ተልዕኳቸውን ለማሳካት ከወረዳ እስከ ሀገሪቱ ከፍተኛአመራርነት የደረሱ እንዳሉም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

   ይሁንና ብዙሀኑ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት፤ የማይወክላቸውን ‘መጂሊስ’ እና የማይቀበሉትን  “አህባሽ”የተባለ አስተምህሮ ፤ከእምነትና ፍላጎታቸው ውጪ እየጫነባቸው ያለው ራሱ መንግስት እንደሆነ፤ ለወራት በዘለቀው የተቃውሞ ሰልፋቸው በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

በመሆኑም ሚኒስትሩ በሥልጠናው ላይ የተናገሩት ነገር፤እንደተለመደው  የሀሰት ክስ በመመስረት ብዙሀኑ ሙስሊም ያነሳውን የመብት ጥያቄ ለማዳፈን የተወጠነ ሴራ ከመሆን የሚያልፍ አይደለም-ሲሉ አንድ የስልጠናው ተሳታፊ ለኢሳት ወኪል ነግረውታል።

ኢቲቪን አስመልክቶ በተነሳው ጥያቄ ዙሪያ በተደረገው ውይይት፤የመንግስት መገናኛ ብዙሀን፤በተለይም ኢቲቪ የብቃትና  የአቅም ማነስ ችግር እንዳለበት ተጠቁሟል።

የመንግስት ጋዜጠኞች፤ የህዝብ ግንኙነት ተግባር ሳይሆን ፤የጋዜጠኝነት ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋል መባሉን የፍኖተ-ነፃነት ዘገባ ያመለክታል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide