በሀረር ከተማ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ወጣቶች ታሰሩ

ማጋቢት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሀረር ባለፈው እሁድ ምሽት የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ ለተቃውሞ አደባባይ የወጣው ህዝብ በፖሊስ ከተበተነ በሁዋላ፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መታሰራቸውን ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል። ከትናናት ጀምሮ ፖሊሶች መንገድ ላይ ያገኙዋቸውን ወጣቶች እያፈሱ እንዲሁም ከቤታቸው እያወጡ ወደ እስር ቤት ወስደዋቸዋል።

በዛሬው እለት በቃጠሎው የደረሰውን ጉዳት አቤት ለማለት የተሰባሰቡ 15 ወጣቶች በፖሊሶች ተይዘው መታሰራቸውን አንድ ወጣት ተናግሯል። ከትናንት ጀምሮ ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ ፖሊሶች መታሰራቸውንም ወጣቱ አክሎአል።

የክልሉ አስተዳዳሪ አቶ ሙራድ አቡደላሂ የተወሰኑ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አምነዋል። የክልሉ ፖሊሶች የእሳት ቃጠለው በደረሰበት አካባቢ በስፋት ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን፣ዘገባውን እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ  የተወሰኑ ትምህርት ቤቶችም ተዘግተዋል።አብዛኛው የከተማው ነዋሪ የእሳት አደጋው መንስኤ የክልሉ መስተዳድር ነው የሚል እምነት ሲኖረው መስተዳድሩ በበኩሉ በህዝቡ የሚቀርበውን ክስ አይቀበልም።

በከተማው ባለፈው እሁድ የተነሳው የእሳት ቃጠሉ ከፍተኛ የንብረት መውደም ማስከተሉ ይታወቃል። ሀረር ከፍተኛ የሆነ የመልካም አስተዳደር እና መሰረታዊ የሆኑ ፍላጎቶች እጥረት እንዳለባት ነዋሪዎች በተደጋጋሚ በምሬት ሲገልጹ ቆይተዋል።