ኢሳት (ሚያዚያ 23 ፥ 2009)
ቅዳሜ ባህርዳር በፈነዳው ቦምብ አንድ ሲቪል ሲገደል አንድ ኢንስፔክተርን ጨምሮ ሶስት የልዩ ሃይል ፖሊሶች መቁሰላቸውን የኢሳት ምንጮች ገለጹ። ዳሸን ቢራ በአዲስ ስያሜ “ባላገሩ” በሚል ራሱን ለማስተዋወቅ በጠራው የሙዚቃ ኮንሰርት አካባቢ በፈነዳው ቦምብ የሙዚቃ ኮንሰርቱ መቋረጡም ታውቋል።
ከፍንዳታው ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች የታሰሩ ሲሆን፣ እስራቱ ይበልጥ በባጃጅ ተሽከርካሪ ሹፌሮች ላይ ያተኮረ እንደሆነም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። የባጃጅ ሹፌሮች ላይ እስራቱ የጠነከረው ቦምቡ ከባጃጅ ውስጥ ተወርውሯል በሚል እንደሆነም ተመልክቷል።
በባህርዳር ከተማ ቅዳሜ ሚያዚያ 21 ቀን 2009 አም የሙዚቃ ኮንሰርት ያቀርባሉ ተብለው ስምና ምስላቸው ከተሰራጨው ታዋቂ ድምጻውያን፣ አርቲስት ኩኩ ሰብስቤ ብቻ የተገኘች ሲሆን፣ አንጋፋው ድምጻዊ መሃመድ አህመድና አርቲስት አረጋኸኝ ወራሽ በዝግጅቱ አልተሳተፉም።
ድምጻዊት ኩኩ ሰብስቤ መድረክ ላይ ወጥታ የሙዚቃ ዝግጅቷን ማቅረብ ስትጀምር ከተሰማው ፍንዳታ ጋር በተያያዘ የሙዚቃ ኮንሰርቱ የተቋረጠ ሲሆን፣ እርሷን ሙዚቃዋን ሳትጨርስ ከመድረክ ወርዳለች። የመግቢያ ዋጋው 50 ብር ብቻ የተጠየቀበት የሙዚቃ ኮንሰርት ቢራ በነጻ የቀረበበት ቢሆን፣ የተገኘው ሰው ከተጠበቀው እጅግ ያነሰ መሆኑም ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በጎንደር ከተማ ትናንት ዕሁድ የተጀመረውን የከተሞች መድረክ ምክንያት በማድረግ በከተማዋ የጸጥታ ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠሉም ተመልክቷል።
በዚሁ ከተማ በተከታታይ የደረሰውን የቦምብ ፍንዳታ ተከትሎ አሜሪካ ዜጎቿ ወደ ጎንደር ከተማ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ የጥንቃቄ ዕርምጃን እንዲወስዱ አርብ ባወጣው መግለጫ ማሳሰቡም ይታወሳል።
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ አራት የቦምብ ፍንዳታዎች መድረሳቸውን ያወሳው በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በአደጋው ቁጥሩ ያልታወቀ ሰው ጉዳት እንደደረሰበትም አስታውቋል።