(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 19/2010)
በስደት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ የተከሰተው የህዝብ ፍጅት እንዲቆም ጥሪ አቀረበ።
መለዮ ለባሽም መሳሪያውን ከሕዝብ ላይ እንዲያነሳ የጠየቀው ቅዱስ ሲኖዶስ የሀገሪቱን ቀውስ ለመፍታት የአደራ መንግስትም እንዲቋቋም ጥሪ አቅርቧል።
በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ “በሀገር ውስጥና በመላው አለም ለምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያን ለምትወዱ ወገኖቻችን” በሚል ርዕስ ጥሪውን አቅርቧል።
ሲኖዶሱ ባወጣውም ጥሪ ኢትዮጵያ የፈተና ደመና እያንዣበባት ነው ሲል አጽንኦት ሰጥቷል።
በኦሮሞና በኢትዮጵያ ሶማሌ ወገኖቻችን ውስጥ ጥቅመኛ ፖለቲከኞች ያቀጣጠሉት ፍጅት በኢትዮጵያውያን መካከል እንኳን ሊደረግ ሊታሰብ የማይችል እንደነበርም በማስታወስ በሁኔታው በእጅጉ ማዘኑን ሲኖዶሱ ገልጿል።
የሀገሪቱ የመከላከያ ሰራዊትና የፖሊስ ሃይል እንዲሁም የደህንነቱ ተቋም የገዛ ዜጎቹን ከማሰቃየት እንዲታቀብም ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው ጠይቋል።
ሁሉም የጸጥታ ሃይሎች ከሕዝቡ ጎን እንዲቆሙም ጥሪ አቅርቧል።
መለዮ ለባሹ የታጠቀውን የጦር መሳሪያ የሀገሩን ድንበር ለማስጠበቅ ያነገበው መሆኑን ተገንዝቦ አፈሙዙን ከሰላማዊ ህዝቡ ላይ ዞር እንዲያደርግ አሳስቧል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የቀጠለውን ችግር ለማስቆምና በሀገሪቱም ዘላቂ መረጋጋት ለማምጣት የአደራ መንግስት እንዲመሰረት ጥሪ ያቀረበው በስደት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተከርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ለተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፣ለምሁራንና ለሃይማኖት መሪዎችም ጥሪ አቅርቧል።
በሀገራችን እየተፈጸመ ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ በዝምታ ማየት ወይንም ይዋል ይደር ብሎ በቸልታ ማለፍ ለስልጣን ሲሉ ከሚገድሉትና ከሚያስሩት የሕወሃት ባለስልጣናት ያነሰ በደል አይደለም ሲል ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጥሪውን አቅርቧል።
በቅዱስ ሲኖዶሱ ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ በአቡነ ጴጥሮስ ስም የወጣው የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ ለትግራይ ሕዝብም ጥሪውን አቅርቧል።
ከመካከላቸው የወጡ ጥቂት ባለስልጣናት የሚሄዱበት መንገድ መልካም ስላልሆነ ከወገናችሁ ሌላው ኢትዮጵያዊ ጎን ተሰለፉ ሲልም ጠይቋል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ ክፉ ቀን እስኪያልፍ ዕርስ በርስ በመረዳዳትና በመተባበር በጸሎትና በምህላ ሀገሩንና ወገኑን እንዲያስብም ቅዱስ ሲኖዶሱ በእግዚአብሔር ስም ጥሪውን ያቀርባል ሲል በመግለጫው ላይ አስፍሯል።
በውጭ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በፓትሪያርክ ብጹእ አቡነ መርቆሪዎስ እንደሚመራ ይታወቃል።