ቁጥራቸው የማይታወቅ እስረኞች በሆስፒታሎች ህክምና እየተደረገላቸው ነው

ኢሳት (ጳጉሜ 1 ፥ 2008)

ሰሞኑን በቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰውን የእሳት አደጋ ተከትሎ የገቡበት ካልታወቀው ወደ ሶስት ሺ አካባቢ እስረኞች መካከል በርካቶች በተለያዩ የአዲስ አበባ ሆስፒታሎች ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ተገለጸ።

የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በበኩሉ ለ8 ሰዓታት ያህል የቆየው የእሳት አደጋ የእስረኞቹን ንብረቶችና መጠለያ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ማውደሙን ማክሰኞ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።

ደርሷል የተባለው የእሳት አደጋ ለስምንት ሰዓታት ያህል መቆየቱ ቢገልፅም፣ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ እሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪዎች በምን ምክንያት እሳቱን ለረጅም ሰዓታት መቆጣጠር እንዳልቻለ የተገለፀ ነገር የለም።

በእስር ቤት ለሰዓታት የቆየ የተኩስ ድምፅ እንደነበር የሚናገሩት እማኞች በበኩላቸው፣ በርካታ ጉዳት የደረሰባቸው እስረኞች ወዳልታወቀ ቦታ ሲጓጓዙ ማየታቸውን አስረድተዋል።

አዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የመንግስት ሆስፒታሎች እነዚሁ እስረኞች ጥበቃ እየተደረገላቸው ህክምና እያገኙ እንደሆነ ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

መንግስት በአደጋው 23 እስረኞች መሞታቸው ይፋ ቢያደርግም የሟቾችን ማንነት ግን ከመግለጽ ተቆጥቦ ይገኛል። የእስረኛ ቤተሰቦች በበኩላቸው ማክሰኞ ድረስ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ሁኔታ ለማወቅ ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን አስታውቀዋል።

የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር እስር ቤቱ ሙሉ ለሙሉ በእሳት አደጋው በመውደሙ ምክንያት እስረኞቹ ወደተለያዩ የፌዴራል እስር ቤቶች መዛወራቸውን ማክሰኞች ቢገልፅም፣ እስረኞቹ የሚገኙበትን ስፍራ ከመግለጽ ተቆጥቧል።

የቤተሰብ አባሎቻቸው የገቡበትን ለማወቅ ተቸግረው የሚገኙ ሰዎች በበኩላቸው፣ መንግስት የሟቾችን ማንነት ይፋ እንዲያደርግና የተቀሩትም ያሉበትን ስፍራ ለጉብኝት ክፍት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የእስረኛ ቤተሰቦች ማክሰኞ በጥቁር አንበሳ፣ ፓውሎስ ሆስፒታልና ሌሎች ሆስፒታሎች በመገኘት የቤተሰብ አባሎቻቸውን ሁኔታ ለማወቅ ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን ከሃገር ቤት የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰውን የእሳት አደጋ ተከትሎ መንግስት መረጃዎችን ይፋ እንዲያደርግ እየጠየቁ ይገኛል።