ጥቅምት ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡባዊ የመን በሻብዋ ግዛት ዋና ከተማ አታቅ ከሚገኘው እስር ቤት ውስጥ ቁጥራቸው ከ1 ሺህ 400 በላይ የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያን እስረኞች ረቡዕ ማለዳ በእስር ቤቱ ጠባቂዎች እርዳታ አምልጠው መውጣታቸውን የአገሪቱ የደኅንነት ባለስልጣናት አስታወቁ።
ሰደተኞቹ በሕገወጥ መንገድ ወደ የመን በመግባታቸው ምክንያት መታሰራቸውን እና ወደ ትውልድ አገራቸው ለመላክ ወደ ማእከሉ መግባታችውን የተደራጁ ታጣቂዎች ከእስር ቤት ጠባቂዎች ጋር በጥምረት በመሆን ወደ አጎራባች ከተሞች ማሪብ እና ባይዳ በተሽከርካሪዎች ጭነው ወስደዋቸዋል ሲሉ ባለስልጣናቱ አክለው ገልጸዋል። ባለፈው ወር ከደቡባዊዋ የወደብ ከተማ ኤደን የባህር ዳርቻ 220 አፍሪካዊያን ስደተኞች ከየመን ወደ ትውልድ አገራቸው መላካቸው ይታወሳል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛሃኞቹ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ነበሩ። በያዝነው ወር ብቻ በእርስበርስ ጦርነት ወደምትታመሰው የመን ከመቶ በላይ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ ባህር ተሻግረው የመን መግባታቸውን ዘኒው አረብ ዘግቧል።