ሼክ አላሙዲን ጋዜጠኞችን ወቀሱ

በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ሳውድ አረቢያዊ የሆኑት ቢሊየነሩ ሼክ አላሙዲን በሸራተን አዲስ ተገኝተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፣ በስፍራው የተገኙትን የመንግስት ጋዜጠኞችና አንዳንድ የግል ሚዲያ ሃላፊዎችን ወቅሰዋል።
ሼክ አላሙዲን በአሜሪካና በአውሮፓ የደሀ መሬት እየወሰዱ ነው እያሉ ስማችንን የሚያጠፉ ስራፈት ሚዲያዎች አሉ ያሉ ሲሆን፣ እናንተም የተባለው ትክክል ነው ወይስ አይደለም ብላችሁ፣ መርምራችሁ ለህዝቡ ማቅረብ ነበረባችሁ በማለት ለዘገባ የተላኩ ጋዜጠኞችን አብጠልጥለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን በሄድኩበት ሀገር ሁሉ አየዋለሁ ያሉት ሼክ አላሙዲ፣ የምታወሩት ስለቻይናና ቱርክ ብቻ ነው፣ እኛ 23 ዓመት ሙሉ የሰራነውን ስራ ግን ሄዶ የሚያይ ጋዜጠኛ የለም ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሚድሮክ በወርቅ ማዕድን ማውጫ ኩባንያው በኩል ባለፉት 16 ዓመታት ከወርቅ ሽያጭ ብቻ 18 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ይፋ አድርጓል። ከዚህ ገቢ ውስጥ ድርጅቱ የከፈለው የግብር መጠን አልተገለጸም።