ሼክ አላሙዲን የህወሃትን 40 ኛ አመት በአል በአዲስ አበባ ስፖንሰር አደረጉ

የካቲት ፲፱(አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በትግራይ ክልል በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር በማውጣት ከአንድ ወር በላይ ሲያከብር የቆየውን የ40ኛ ኣመት የምስረታ በዓሉን የፊታችን እሁድ በአዲስአበባ ሚሌኒየም አዳራሽ በሚያካሂደው ድግስ ለማጠቃለል መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡

በዚህ ዝግጅት ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ አምባሳደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሚገኙ ሲሆን የዕለቱን የፌሽታ  በዓል ወጪ ሚሊየነሩ ሼህ አልአሙዲ እንደሚሸፍኑት ምንጮች ገልጸዋል። ህወሓት 40ኛ ዓመት በዓሉን አስታኮ ያለእሱ ሀገሪትዋ ምንም አማራጭ እንደሌላት በመስበክ አጋጣሚውን በመንግስት ሐብት፣ ንብረትና ገንዘብ ለምርጫ ቅስቀሳ እየተጠቀመበት ነው በሚል አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርጊቱን ማውገዛቸው የሚታወስ ነው፡፡

አርቲስቶችና ጋዜጠኞችን የትግራይ ክልል የሚገኘውን የደደቢት በርሃ ከአንድ ወር በፊት በማስጎብኘት የተጀመረው የህወሃት 40ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እጅግ በተጋነነ መልኩ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት ከመንግስት ካዝና ወጪ ሆኖ በፌሽታ ሲከበር መሰንበቱ ይታወሳል፡

በዚህ በዓሉ ላይ የህወሓት መመስረት ለሀገሪቱ ትንሳዔ እንዳስገኘ ፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ፣ የህግ የበላይነት እንደተገኘ ተደርጎ በመንግስት ቁጥጥር ስር ባሉ መገናኛ ብዙሃን የአንድ ፓርቲ ፕሮፖጋንዳ ሲሰራጭ ይሰንብት እንጂ በተቃራኒው የትግራይ ሕዝብን ጨምሮ መላው ሕዝብ በህወሓት መራሹ መንግስት ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የዴሞክራሲና የፍትሕ መጓደል እንዳንገሸገሸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ጠቅሰው ይህ ሁኔታ ህወሓቶች ከሕዝቡ የቱን ያህል እንደራቁ ትንሽ ማሳያ ነው ብሎአል፡፡