ሸቀጦች በሬሽን ኩፖን መሸጥ ጀመሩ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 17/2010) በቀበሌ ሕብረት ሱቆች በኮታ እየተሸጡ ያሉ ሸቀጦች ህገ ወጥ በሆነ መንገድ አየር በአየር እንደሚቸበቸቡ ነዋሪዎች ገለጹ።

ሸቀጦቹን ለመግዛት ሙሉ ቀን የሚያዘው ወረፋ አሰልቺ መሆኑንም ነዋሪዎቹ በምሬት ተናግረዋል።

የኢሳት የአዲስ አበባ ወኪል በቀበሌ ሕብረት ሱቆችና ሸማቾች ማህበራት ተዟዙሮ እንደተመለከቱው  ነዋሪዎች በሬሽን ኩፖን በኮታ መልኩ ስኳር፣ዘይትና የመሳሰሉትን ሸቀጦች ለመግዛት በእኩለ ለሊት በመነሳት ወረፋ መያዝ ግዴታቸው ሆኗል።

ሸቀጦቹንም ለመግዛት ሙሉ ቀን በሰልፍ  ማሳለፍም እየተለመደ መጥቷል።

ነዋሪዎቹ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን በተሰጣቸው ሬሽን ኩፖን ለመግዛት ቀኑን ሙሉ ቢንገላቱም  የማይሳካበት  ሁኔታ  እንዳለም መረዳት ተችሏል።እንደ ስኳር፣ዘይትና ዱቄት የመሳሰሉ ምርቶች  በሕገወጥ መንገድ አየር በአየር ለአትራፊ ድርጅቶች  ሰለሚተላለፉ እንዲሁም ዕጥረት በመኖሩ  ተጠቃሚዎች ሳይደርሳቸው  የሚቀርበት ሁኔታ መኖሩንም መረዳት ተችሏል።

በኮታ ለነዋሪው የሚቀርቡ ምርቶች ሕብረት ሱቅና የሸማቾች መደብር ሳይደርሱ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ወደ ገበያ በመሻገራቸው የዋጋ ግሽበቱን እንዳባባሰው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በሌላም በኩል የግለሰቦች ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ዜጎች የወረዳው መስተዳድርም ሆነ የሕብረት ሱቆች ራሽን ካርድ ስለማይሰጧቸው ከሌላው ነዋሪ በሁለት እጥፍ ከአትራፊዎች ለመግዛት መገደዳቸውን ተናግረዋል።

በአንድ ወር ውስጥ የዘይት ዋጋ ለሶስት ያህል ጊዜ በተካሄደ ጭማሪ የገዙ የግለሰብ ቤት ተከራዮች ኩፖን ወይንም ራሽን ካርድ አሰጣጡ ፍትሃዊነት የጎደለው እንደሆነ ተናግረዋል።