ኢሳት (ግንቦት 22 ፥ 2008)
በሶማሊያ ሞቃዲሾና ጌዶ በተባሉት አካባቢዎች ሁለት የሶማሊያ ዜጎችና ሌሎች ሶስት ኢትዮጵያውያን በመንገድ ዳር በተጠመደ የተሽከርካሪ ፈንጅ መገደላቸው ተነገረ።
ኢትዮጵያውያኑ ወታደሮች የተገደሉት የርቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያ በተገጠመለት የመንገድ ዳር ፈንጅ ጌዶ በሚባል አካባቢ ሲሆን፣ በሶማሊያ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው አልሻባብ የተባለው ቡድን ሃላፊነት መውሰዱን ማሪግ የተባለው በሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚዘግበው ድረገጽ ዘግቧል። አልሻባብ የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ወታደሮች በሶማሊያ የአፍሪካ አንድነት የሰላም አስከባሪ ሃይል ሰራተኞች እንደነበሩ አክሎ ገልጿል።
በጌዶ አካባቢው በሚገኝ ዩርኩድ በተባለው በርቀት መቆጣጠሪያ በፈነዳው በዚሁ የፈንጅ ጥቃት፣ ኢትዮጵያውያን ወታደሮችን ጭኖ የነበረ ወታደራዊ ተሽከርካሪ መቃጠሉንም የአልሻባብ ድረገጽን ዋቢ በማድረግ ማሪግ የተባለው ድረገጽ ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶማሊያ ብሄራዊ ደህንነት ድርጅት ሰራተኞችን ከሞቃዲሾ ከተማ ሲንቃ-ድኸር ወደሚባል አካባቢ ጭኖ ሲጓዝ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ በደረሰ አደጋ ሁለት የደህነነት ሰራተኞች መሞታቸው ተገለጸ። ጥቃቱ የደረሰው በመንገድ ዳር በተጠመደው ፈንጅ እንደሆነ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ በአካባቢው የሚኖሩት የአይን እማኞችን ጠቅሶ ማረግ የተባለው ድረገጽ ዘግቧል።
ባለፈው ቅዳሜ በደረሰው በዚሁ ጥቃት ሃላፊነት የወሰደ ቡድን ባይኖርም፣ ጥቃቱን ምን አልባት አልሻባብ አድርሶት ሊሆን እንደሚችል በአካባቢው ላይ ጥናት ያደረጉ ተንታኞች ይገልጻሉ።