መስከረም ፪(ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከምእራባዊያን አገራት በተለይም ከአሜሪካ ድብደባ ለጊዜውም ቢሆን የተረፈችው ሶሪያ በአገሯ ያሉ የኬሚካል የጦር መሳሪያዎችን በሙሉ ለማውደም ፈቃደኛ መሆኑዋን ፕሬዚዳንት በሽር አላሳድ ተናግረዋል።
ከሩሲያ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት አላሳድ፣ አገራቸው ስምምነቱን የምትፈርመው ሩሲያ ስላግባባቻች እንጅ የአሜሪካን ጥቃት ፈርታ አይደለም።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን በኒውዮርክ ታይምስ ላይ ለአሜሪካ ህዝብ እንዲደርስ በማለት ባሰፈሩት ጽሁፍ አሜሪካ በሶሪያ ላይ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ ሽብርተኝነት እንደሚስፋፋና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ተናግረዋል።
ሶሪያ ያላትን የጦር መሳሪያ በሙሉ ለማውደም እንድትስማማ ሩሲያ ከፍተኛውን ሚና ተጫውታለች። ፕሬዚዳንት አቦማ በሩሲያ የቀረበውን ሀሳብ በመቀበል ለዲፕሎማሲ እድል ለመስጠት መስማማታቸውን ገልጸዋል።
የሩሲያና አሜሪካ የውጭ ግንኙነት ሀላፊዎች ጄኔቭ ላይ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘዋል። በኒዜርላንድስ ሄግ ከተማ የሚገኘው የተመድ የኬሚካል አጣሪ ቡድን ሪፖርተሩን በመጪው ሳምንት ውስጥ ሊያቀርብ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።