ኢትዮጵያ እና ሶማሊያዊ ስደተኞችን ይዞ ይጓዝ የነበረ ጀልባ ሰጥሞ 112 ስደተኞች ሞቱ

ኢሳት (ጥር 2 ፥ 2008)

በጎረቤት ሶማሊላንድ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያዊ ስደተኞችን ይዞ ይጓዝ የነበረ ጀልባ የመስጠም አደጋ አጋጥሞት በትንሹ 112ቱ መሞታቸውን የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ሰኞ አስታወቁ።

ራሷን ነጻ ሃገር አድርጋ ባወጀችው ሶማሊላንድ በደረሰው የጀልባ አደጋ የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩንም የነብስ አድኑ ሰራተኞች ገልጸዋል።

በጀልባው ላይ ከደረሰው አደጋ 75 ሰዎችን መታደግ እንደተቻለና ስደተኞቹን ይዞ ይጓዝ የነበረው ጀልባ የቴክኒክ ችግር አጋጥሞት እንደነበር የሶማሊላንድ የክልል የጤና ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አብዱራህማን ያሲን ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

በዚሁ አደጋ በትንሹ 112 ሰደተኞች የሞቱ ቢሆንም ከእነዚሁ መካከል ስንቶቹ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ የታወቀ ነገር የለም።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ስደተኞች በርበራ የወደብ ከተማ የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚገኝ ሲሆን የጀልባው ሶስት ሰራተኞች ለማምለጥ ሙከራ ሲያደርጉ በቅጥጥር ስር መዋላቸውንም የሶማሊላንድ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ሰራተኞችን ይዞ ይጓዝ የነበረው ጀልባ ወደ የመን በማቅናት ላይ እንደነበርም ተነግሯል።

በየጊዜው በርካታ ኢትዮጵያን በሶማሊላንድ በኩል በማድረግ ወደ የመንና ሌሎች ጎረቤት ሃገራት በመሰደድ ላይ መኖናቸውን የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጀት (IOM) መረጃ ያመለክታል።

ባለፈው አመትም ከ70 በላይ  የሚሆኑ ኢትዮጵያን በጀልባ አደጋ በሶማሊላንድ መሞታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።