ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በቃሊቲና በሌሎች የኢትዮጵያ ወህኒ ቤቶች የደረሰባቸውን ሰቆቃ ገለጹ

ኢሳት (ሚያዚያ 12 ፥ 2008)

የህወሃት ኢህአዴግን መንግስት በመሸሽ በኬንያ ተሰደው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በቃሊቲና በሌሎች የኢትዮጵያ ወህኒ ቤቶች የደረሰባቸውን ሰቆቃ ኦኬ አፍሪካ ለተባለ ጋዜጣ በዝርዝር ገለጹ።

በኢትዮጵያ ወህኔ ቤቶች ምን አይነት ሰቆቃ በእስረኞቹ ላይ ሲደርስ እንደበር በዝርዝር ያሰፈረው ጋዜጣው፣  በኬንያ ያሉት ስደተኞች በኢትዮጵያ ውስጥ ታስረው በነበሩበት ጊዜ፣ በማዕከላዊና በሌሎች ተመሳሳይ እስር ቤቶች የሚገኙ መርማሪዎች፣ እስረኞቹን በኤለክትሪክ ወንበር እንደሚያቃጥሉ፣ እስኪቆስሉ ከገረፉ በኋላ በግርፋት ብዛት በሚደማ ሰውነት ላይ በረዶ ውሃ እንደሚያፈሱ፣ በቀዝቃዛ ኮንክሪት ወለል ላይ ራቁታቸውን እንደሚያስተኟቸው፣ በወንድ ብልት ላይ ጠርሙስ አንጠልጥለው እንደሚያውሉ፣ እንዲሁም መሳሪያ በመደገን፣ አይንን በመሸፈን ግድያ እንፈጽምባችኋለን በማለት እንደሚያስፈራሩ ተጎጂዎችን ዋቢ በማድረግ ኦኬ አፍሪካ ሃተታውን ቀጥሎ እንዲህ አይነት አሰቃቂ ድርጊት የተፈጸመባቸው ኢትዮጵያውን በኬንያ የጥገኝነት ጥያቄ ቢጠይቁም፣ አንዳንዶቹ ተገቢ ጥበቃና እንክብካቤ አያገኙም ሲል ጋዜጣው ዘግቧል።

ከዚህ በፊት በአገር ውስት የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትም በእስር ቤት ቆይታቸው ከፍተኛ ሰቆቃ ሲፈጸምባቸው እንደነበር መዘገባቸው ይታወሳል። ባለፈው መጋቢት ወር የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ዘመነ ምህረቱ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ በማዕከላዊ እስር ቤት የህወሃት መርማሪዎች ከፍተኛ አካላዊና ሞራላዊ ሰቆቃ በእርሳቸው ላይ ሲፈጽሙባቸው እንደቆዩ መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

አቶ ዘመነ ምንም ወንጀል ባልፈፀሙበት ሁኔታ ከጎንደር ተይዘው አዲስ አበባ እስኪደርሱ ድረስ አይናቸው ተሸፍኖ፣ እግራቸውና እጃቸው ተጠፍሮ እንደተሰቃዩና በህወሃት/ኢህአዴግ እስር ቤት እያሉም የህወሃት ገራፊዎች ሱሪያቸውን አስልወልቀው፣ በላያቸው ላይ ሽንት እንደሸኑባቸው፣ አስጸያፊ የዘር ስድብ  እንደሰደቧቸውና ከፍተኛ ድብደባ እንደፈጸሙባቸው አቶ ዘመነ ምህረቱ ገልጸዋል።