ጥቅምት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ሽብርተኝነትን በመርዳት ክስ ተመስርቶባቸው ላለፈው አንድ ዓመት በ ኢትዮጵያ ከታሰሩ በሁዋላ በቅርቡ በይቅርታ የተለቀቁት ሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች በሽልማት ያገኙትን 10 ሺህ የስዊድን ክሮነር በቃሊቲ እስር ቤት በዞን ስድስት ውስጥ ላሉ እስረኞች ለማበርከት ወሰኑ።
በ እስር ቆይታቸው የኢትዮጵያውያንን አብሮ የመብላት ባህል ማየታቸውን የገለፁት ማርቲን ሽብዬ እና ጆሀን ፔርሰን፤ 10 ሺህ ክሩነሩን የለገሱት፤ የኢትዮጵያ ዓመት በዓል ሲመጣ አብረዋቸው ታስረው ለነበሩት በዞን ስድስት ላሉ እስረኞች በሬ እንዲገዛላቸው ነው።
ሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ነበር በሶማሌ ክልል እየተፈፀመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመዘገብ ከ ኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ጋር በመሆን ወደ ጂጂጋ ለመግባት ሲሞክሩ በ ኢትዮጵያ ወታደሮች የተያዙት።
ሰሞኑን በይቅርታ ከለቀቁ በሁዋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በ ኢትዮጵያ እስር ቤት በታሳሪዎች ላይ እየተፈፀመ ነው ያሉትን የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማጋለጣቸው ይታወሳል።
<<እኛ ከ እስር ቤት ልንወጣ አንድ ቀን ሲቀረን ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እጆቻቸውን በካቴና የፊጥኝ እንደታሰሩ”ማርቲን፤ ጆሀን>በማለት በስማችን ከጠሩን በሁዋላ<፤<አደራ!አደራ! እየተፈፀመብን ያለውን ነገር ለ ዓለማቀፉ ህብረተሰብ አሳውቁልን!” በማለት አደራ ሰጥተውናል ያሉት ሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች፤ የነሱ አደራ ስላለባቸው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የ ኢትዮጵያ መንግስት እየፈፀመው ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለ ዓለማቀፉ ህብረተሰብ ማጋለጡን እንደሚገፉበት አስታውቀዋል።
በስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች ድርጊት የተቆጣው የ ኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰሞኑን ባወጣው ረዥም መግለጫ ጋዜጠኞቹ በምህረት ከተለቀቁ በሁዋላ በ ኢትዮጵያ መንግስት ላይ እያሰሙት ያለውን ክስ ተቃውሞአል።