(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 11/2010) ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ራሱ በኢትዮጵያውያን ላይ የሽብር ድርጊት ሲፈጽም መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ።
መከላከያና ደህንነቱ ከፖለቲካ ፓርቲ ነጻ እንዲሆን ሕገ መንግስቱ ቢያዝም በተግባር ግን ይህ ሳይፈጸም መቆየቱንም ይፋ አድርገዋል።
ግንቦት 7፣ኦነግና ኦብነግ ግዜ ካለፈበት የመሳሪያ ትግል ራሳቸውን አቅበው ወደ ሰላማዊ መድረክ እንዲመለሱ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ዶክተር ብርሃኑ እኔን ገድለው ወይንም አስገድለው ስልጣን ቢይዙ እኔም እሳቸውን ብገድል ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ጉዳይ አይደለም ሲሉ አመልክተዋል።
በአሸባሪነት የታሰሩ ሰዎች የሚፈቱበትን ሁኔታ በተመለከተ ዛሬ በፓርላማው ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሽብር ምንድን ነው አሸባሪስ ማነው የሚለውን በማብራራት ምላሻቸውን ጀምረዋል።
ሕገ መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ ስልጣንን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ አሸባሪነት ከሆነ ሕገ መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚደረገውስ አካሄድ ምን ይባላል ሲሉ መልሰው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሕገ መንግስቱ እስረኛ ግረፉ፣እስረኛ ጭለማ ቤት አስገቡ ይላል ወይ ሲሉ ለፓርላማው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
ይህ የማንም ሳይሆን የእኛ አሸባሪነት ተግባር ነው ሲሉ ገልጸውታል።
የመከላከያ ሰራዊቱና ደህንነቱ ከፖለቲካ ፓርቲ ነጻ መሆን እንዳለበት በህገ መንግስቱ መደንገጉንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታውሰዋል።
በተግባር ግን ይህ ስራ ላይ አለመዋሉን በመጥቀስ የስርአቱን የህገወጥነት ጉዞ አሳይተዋል።
ግንቦት 7፣ ኦነግና ኦብነግ ግዜ ያለፈበትን የትጥቅ ትግል ትተው ከኤርትራ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መገዳደል እንዲያበቃም ጥሪ አቅርበዋል።
ዶክተር ብርሃኑ እኔን ገድለው ወይንም አስገድለው ስልጣን ላይ ቢወጡ እኔም እሳቸውን ገድዬ ስልጣን ላይ ብቆይ ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት አይደለም ሲሉም አስምረውበታል።
በሽብር ታስረው የተፈቱ ሰዎችን በተመለከተ ለተነሳባቸው ጥያቄም ሕዝቡ ለእኛ ይቅርታ እንዳደረገው ለነርሱም መንግስት ይቅርታ ያደርጋል ብለዋል።
የሕዝቡም ምላሽ ታይቷል ብለዋል።