(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 16/2009) ስልጣን ላይ ያለውን አገዛዝ በማስገደድ ወይንም በማስወገድ በኢትዮጵያ የስርአት ለውጥ ለማምጣት ሕዝብን ያማከለ ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮጵያ ሕልውና ከምንጊዜውም በላይ በፈተና ውስጥ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅትም የተቃውሞ ሃይሎችም መተባበር እንደሚገባቸው አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ከነሐሴ 12 እስከ 14/2009 በዩኤስ አሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት አሌክሳንድሪያ ከተማ ባካሄደው 4ኛ ጉባኤ ማጠቃለያ ባወጣው በዚህ መግለጫ በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰቱና የቀጠሉ ችግሮችን በዝርዝር ተመልክቷል።
ለሀገራችን ችግር ተመራጩ መንገድ እርቅ መሆኑን አመልክቶ ለዚህም ስርአቱን በመወጠር ወደ እርቅ ማምጣት ካልሆነም ከስልጣን በማስወገድ የስርአት ለውጥ ለማምጣት መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝቧል።
የሶስት ቀናት ጉባኤውን በቨርጂኒያ ግዛት አሌክሳንድሪያ ከተማ ያካሄደው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ባወጣው ባለ 4 ገጽ መግለጫ ለተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥሪ አቅርቧል።
በዚህም ወጣቱ ለለውጥ እንዲንቀሳቀስና ከሸንጎ ጎን እንዲሰለፍ እንዲሁም የተቃዋሚ ሃይሎች እንዲተባበሩና ስርአቱን እያገለገሉ ያሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ፖሊሶችና የደህንነት ሰራተኞች ከሕዝብ ጎን በመሰለፍ ከታሪክ ተጠያቂነት ነጻ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።
ሕወሃት ጎጠኛና አሸባሪ ቡድን በመሆኑ የትግራይን ህዝብ ሳይሆን የራሱን ጥቅም ነው የሚያስከብረው ያለው የሸንጎው መግለጫ የትግራይም ሕዝብ የህንን ተረድቶ ከኢትዮጵያዊ ወገኑ ጎን እንዲሰለፍና በስሙ በሚነግደው አገዛዝ ላይ እንዲነሳ ጥሪ አቅርቧል።
በመጨረሻም ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ባቀረበው ጥሪም በኢትዮጵያ ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ሁለንተናዊ ጭቆናና የሰብአዊ መብት ረገጣ በመቃወም የኢትዮጵያ ሕዝብ እያካሄደ ያለውን ትግል እንዲደግፍም ጥይቋል።