ኢሳት (የካቲት 8 ፥ 2009)
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ስልሳ የመንግስት ልማት ድርጅቶች በኪሳራ ሊዘጉ መሆኑን የመንግስት ልማት ድርጅቶች ባለአደራ ቦርድ አስታወቀ።
ባለፉት 15 አመታት ወደ ግል ከተዛወሩ 263 የመንግስት ልማት ድርጅቶች ውስጥ በ60 ድርጅቶች ስም የነበሩ ተሰብሳቢና ተከፋይ ዕርምጃዎች ማግኘት ባለመቻሉ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ እንደሚሰርዝ የቦርዱ ሃላፊዎች ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት መንግስታዊ ቦርድ የ60 ዎቹን የልማት ድርጅቶች ሂሳብ እያጣራ ሲሆን፣ የአቃቂ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ቡና ላኪዎች ማህበርና ተዋህዶ ጥበብ ፋብሪካን ሂሳብ አጣርቶ በማጠናቀቁ ሙሉ ለሙሉ መሰረዛቸውን የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ፈፋኝ ዋቢ በማድረግ ሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ዘግቧል።
በኪሳራ የሚዘጉት 60 ድርጅቶች ግን እንደሚሰርዙና ለማፍረስ በሂደት ላይ መሆናቸውን የቦርድ ሃላፊዎች አስረድተዋል።
መንግስታዊ ቦርድ በጥቁር አባይ ኮንስትራክሽን እና በብሄራዊ መሃንዲሶችና ተቋራጮች ማህበር ላይ የሂሳብ ማጣራት ሂደቱ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታውቆ፣ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ያለባቸው እዳ እንደሚሰረዝም አክሎ አመልክቷል።
ወደ ግል ከተዛወሩ በርካታ መንግስታዊ የልማት ድርጅቶች መንግስት መሰባሰብ የነበረበት በመቶ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብም ሳይሰበሰብ መቅረቱን ለመረዳት ተችላል። ይዞታቸው ተሰርዞ ይፈርሳሉ የተባሉት 60 ድርጅቶች በተለያዩ የሃገሪቱ ስፍራዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በተቋሙ ጊዜ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ መደረጉ ታውቋል።
እነዚሁ ይፈርሳሉ የተባሉ የመንግስት ተቋማት ንብረት ሜቴክ ለተባለው የመከላከያ ተቋም ለምስጠት ዝግጅት መድረጉን ምጮች ገልጸዋል።
በህወሃቱ ታጋይ ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የሚመራው ሜቴክ ከኢትዮጵያ መንገዶች በለስልጣን እጠግናለሁ ብሎ የወሰደውን የ65 ሚሊዮን ብር ማሽነሪ ለትግራይ ክልል ውሃ ስራዎች በስጦታ በመስጠቱ ውዝግብ ማስነሳት ይታወሳል።