ሴኔጋል የጋምቢያውን ፕሬዚደንት ከስልጣን ለማስወገድ ወታደሮቿን ወደ ሃገሪቱ ልታሰማራ ነው

ኢሳት (ታህሳስ 14 ፥ 2009)

ሴኔጋል የጋምቢያው ፕሬዚደንትን በወታደራዊ ዕርምጃ ከስልጣን ለማስወገድ ወታደሮቿን ወደ ሃገሪቱ ልታሰማራ መሆኑ ተገለጸ።

የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ተወካዮች ፕሬዚደንት ያህ’ያ ጃም’ህ የምርጫ ሽንፈታቸውን ተቀብለው ከስልጣን እንዲወርዱ ማግባባትን ቢያደርጉም፣ ፕሬዚደንቱ ለሃገራት ተወካዮች አሻፈረኝ ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በሃገሪቱ ተወካዮች ሲካሄድ የቆየው ድርድር ውጤት አለማምጣቱን ተከትሎም የቀጠናው ሃገራት ሴኔጋል ወታደራዊ ዕርምጃውን እንድትወስድ ሃላፊነት መስጠታቸው ታውቋል።

ሴኔጋል በበኩሏ ወታደሮቿ ለዘመቻው እንዲዘጋጅ ልዩ ትዕዛዝ የሰጠች ሲሆን፣ የጋምቢያው ፕሬዚደንት የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ሃገራት በሃገራቸው ጣልቃ የመግባት ስልጣን የላቸውም ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል።

ትንሿ ምዕራባዊቷ አፍሪካ ለ22 አመታት የመሩት ፕሬዚደንት ያህ’ያ የምርጫ ሽንፈታቸውን ከተቀበሉ በኋላ በሰዓታት ልዩነት ምርጫው በትክልል አልተካሄደም በማለት ውጤቱን እንዳማይቀበሉ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ይሁንና የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን የተካሄደው ምርጫ ምንም ግድፈት እንዳልነበረበት በመግለጽ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሩ አዳማ ባሮው አሸናፊ መሆናቸው ተገልጿል።

የቀጠናው የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ሃላፊ የሆኑት ማርሴል አሌን ዴሱዛ የጋምቢያው ፕሬዚደንት በቀጣዮቹ 25 ቀናት ውስጥ ስልጣናቸውን የማይለቁ ከሆነ ወታደራዊ ዕርምጃውን የማይቀር መሆኑን ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

እንደፈለጉት ያዙታል በተባለው የጋምቢያው የበላይ ፍርድ ቤት በምርጫው ሂደት ላይ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ፕሬዚደንት ያህ’ያ ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ የጠየቁ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም ከአንድ ሳምንት በኋላ ውሳኔውን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።