ሴቶች ያልተሳተፉበት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስረታ ስኬታማ አይሆንም ተባለ

መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ግማሽ ህዝብ የሚሆኑትን ሴት እህቶቻችን ያልተሳተፉበት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስረታ ስኬቱ ያማረ እንደማይሆን፣ ቢሆንም ራሱን ለጥፋት እንደሚያጋልጥ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ተናገሩ።

 አቶ ኦባንግ ይህን የተናገሩት፤  ሰሞኑን ከየካቲት 30 እስከ መጋቢት 3 ቀን  በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የኢትዮጵያ ሴቶች ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ  ነው።

 “የሴቶችን መብት በማስከበር ለሥልጣን ማጎናጸፍ” በሚል ርዕስ  አቶ ኦባንግ ባደረጉት በዚህ ንግግር  ለዛሬው ለርእሳቸው ማንነት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉላቸው ሴት አያታቸው መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ለሴት እህቶችና እናቶች አስፈላጊው ክብርና ዋጋ ሊሰጥ እንደሚገባ አሣስበዋል።

“ሴቶች እህቶቻችንን ያላሳፈረ የነፃነት፣ የሠላምና የብልጽግና ባቡር ከታሰበለት የነፃነት ጣቢያ ሊያደርስ አይችልም” ሲሉም አቶ ኦባንግ አክለዋል።

 “አገራችን ሁሉም ዓይነት ሴቶች ያስፈልጓታል። አምላክ ለዚህ የተቀደሰ ተግባር የጠራው የተማሩትንና የተሻሉትን ብቻ አይደለም። ሁሉንም እንጂ! ስለዚህም በኦሞ ሸለቆ ከንፈሮቿ ላይ ሸክላ ከምታንጠለጥለው ውብ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከንፈሮቿን ቀይ ቀለም እስከተቀባችው ቆንጆ፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ባዶ እግሯን ከተዋበችው ጀምሮ በዋንዳቢቲ እስካጌጠችው የኦሮሞ ኮረዳ፤ በኦጋዴን በሒጃብ ካሸበረቀችው ኢትዮጵያዊት ጀምሮ ባማረ ጥለት እስከተዋበችው የአማራ ቆንጆ፤ ግማሽ አካሏ እርቃን ከሆነው የአፋር ድንቅ ጀምሮ በሹርባዋ እስከተዋበችው የትግራይ ሴት … ሁሉም ዓይነት ሴቶች ኢትዮጵያችን ያስፈልጓታል።” ብለዋል አቶ ኦባንግ ።

በማያያዝም በጉባዔው ላይ እየተሳተፉ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ሴቶች፦ “እነዚህ ሴቶች እናንተ ናችሁ፤ እናንተም እነዚያ ሴቶች ናችሁ። እናንተ እዚህ የተሰበሰባችሁ አገር ቤት ያሉት ሴቶች ሁሉ ተወካዮች ናችሁ። አገር ቤት ያሉት ኢትዮጵያውያን ሴቶች መብት እስካልተከበረ ድረስ የእናንተ በምዕራባውያን አገራት መብታችሁ መከበሩ ብቻ በቂ አይሆንም።” በማለት  ለጋራ ትግል መልዕክት አስተላልፈዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide