(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 10/2010)
ሳውዳረቢያ ከሃውቲ አማጽያን የተተኮሰባትን ባሊስቲክ ሚሳኤል ሪያድ አቅራቢያ ማምከኗን አስታወቀች።
የሃውቲው አል ማሲራህ ቴሌቪዥን እንዳለው በአማጽያኑ የተተኮሰው ሚሳኤል በአል-ያማማ ቤተመንግስት በስብሰባ ላይ የነበሩ የሳውዲ መሪዎችን ኢላማ ያደረገ ነበር።
ሳውዳረቢያና አሜሪካ ኢራን የሃውቲ አማጽያንን ሚሳኤል ታስታጥቃለች ሲሉ ይከሳሉ።
ኢራን ግን ክሱን ታስተባብላለች።
ባለፈው ወርም ተመሳሳይ ሚሳኤል የሪያድን አይሮፕላን ማረፊያ ሊመታ ጥቂት ሲቀረው ነበር ተጠልፎ የወደቀው።
የሃውቲ አማጽያን ላለፉት 3 አመታት የየመንን መንግስትና በሳውዲ የሚመራውን ግንባር እየተፋለሙ ይገኛሉ።
የሃውቴ አል -ማሲራ ድረ-ገጽ እንዳሰፈረውም ቡርካን ሁለት በመባል የሚታወቀውን ሚሳኤል ዛሬ ከቀትር በኋላ አማጽያኑ ማስወንጨፋቸውን ይፋ አድርጓል።
ይህም ይላል ድረ-ገጹ አሜሪካና ሳውዲ በየመን ሕዝብ ላይ ለፈጸሙት ወንጀል የተሰጣቸው መልስ ነው።
ድረ-ገጹ ሲቀጥልም ሚሳኤሉ ኢላማ ያደረገው በአልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን በሚመራውና በሳውዲ አመታዊ በጀት ላይ እየተወያየ ባለው የባለስልጣናት ስብሰባ ላይ ነበር።
ኢላማ የተደረገውና አል-ያማማ የተሰኘው ቤተመንግስት የንጉሱ ዋና ቢሮና ንጉሳዊው ፍርድ ቤት የሚገኝበት እንደሆነም ታውቋል።
በሳውዲ መንግስት የሚተዳደረው አል-አክባሪያ የተሰኘው ቴሌቪዥን ሚሳኤሉ ከመዲናዋ ሪያድ ደቡብ አቅራቢያ መምከኑን አረጋግጧል።
ሳውዲ በአሜሪካ የተሰጣት ፔትሪየት የተሰኘ የጸረ ሚሳኤል ቴክኖሎጂ ባለቤት ስትሆን ባለፈው ወር የአውሮፕላን ማረፊያውን ኢላማ ያደረገውንና በሃውቲ የተተኮሰውን ሚሳኤል በዚሁ ጸረ ሚሳኤል መትቼ ጥያለሁ ብትልም ወታደራዊ ተንታኞች ግን ሚሳኤሉ የአውሮፕላን ማረፊያው የሀገር ውስጥ ተርሚናል አቅራቢያ እንዳረፈ ይናገራሉ።
የየመን የቀድሞ ፕሬዝዳንት አሊ አብደላህ ሳላህ ከሁለት ሳምንት በፊት ለጊዜውም ቢሆን አጋራቸው በነበሩት ሀውቲ አማጽያን መገደላቸው ሲታወስ በየመን እየተካሄደ ባለው ጦርነት እስካሁን ወደ 9ሺ የሚጠጉ ሰዎች ሲሞቱ ወደ 50ሺ ደግሞ ቆስለዋል።