ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2008)
የጣሊያኑ ኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሳሊኒ) በኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ አካባቢ ኣያካሄደ ያለው የግድብ ግንባታ በኢትዮጵያና ኬንያ የድንበር ዙሪያ በሚኖሩ ማህበረሰቦች ላይ የረሃብ አደጋ መፈጠሩን ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል የተሰኘ አለም አቀፍ ተቋም ማክሰኞ ገለጠ።
በስፍራው በመካሄድ ላይ ያለው የግድብ ግንባታ የቱርካና ሃይቅ የውሃ መጠን እንዲቀንስ በማድረጉ በሺዎቹ የሚቆጠሩ የካሮ ጎሳ አባላት ለረሃብ መጋለጣቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።
በግልገል ጊቤ ሶስተኛ የሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ምክንያት በአካባቢው እያደረሰ ነው ያለውን ጉዳት ለአለም አቀፍ የኢኮኖሚና የትብብር ድርጅት ያቀረበው ሰርቫይባል ኢንተርናሽናል በቱርካና ሃይቅ ላይ ህይወታቸው የተመሰረተ ከ100ሺ በላይ የማህበረሰቡ አባላት ለችግር መጋለጣቸውንም አመልክቷል።
የጣሊያኑ ኩባንያ ለነዋሪዎች ሰው ሰራሽ የውሃ ማዳረሻ አገልግሎት ይሰራል ብሎ ቃል ቢገባም በካሳ መልክ ያቀረበው እቅድ ተግባራዊ አለመሆኑን ይኸው በጎሳዎች መብት መከበር ዙሪያ የሚሰራው ተቋም ገልጿል።
የጣሊያኑ የኮንስትራክሽን ኩባንያ የገባው ቃል በማፍረስና እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን ችላ በማለት በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ህይወት አደጋ ላይ ጥሏል ሲሉ የሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል ድርጅት ሃላፊ ስቴፈን ኮሪ መግለጻቸውን ታይምስ ላይቭ የተሰኘ መጽሄት ዘግቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት እያካሄደ ያለው የልማት ፖሊሲ አሉታዊ አስተዋጽዖው የጎላ ሆኗል ያሉት ሃላፊው፣ ምዕራብያውያን ያሳዩት ድጋፍና ዝምታም ችግሩን ማባባሱን አስረድተዋል።
የነዋሪዎችን መሬት መዝረፍና በአካባቢ ላይ ጥፋትን ማድረስ እድገትን ሳይሆን በማህበረሰቡ ላይ የሞት ቅጣትን እንዲያስተላልፍ ነው ሲሉም ስቴፈን ኮሪ አክለው አስታውቀዋል።
የኬንያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች በበኩላቸው የሃገራቸው መንግስት በቱርካና ሃይቅ ላይ የሚደረሰውን ጉዳት ችላ ብሎታል በማለት ተደጋጋሚ ቅሬታን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
ጉዳዩ የአለም አቀፍ የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ድርጅት ያቀረበውን ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል 34 ሃገራትን በአባልነት የያዘው ተቋም ለአቤቱታው አስቸኳይ ምላሽን እንዲሰጥ መጠየቁንም ለመረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት የግድቡ ግንባታ በአካባቢው ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ የለም በማለት እያቀረቡ ያሉ አቤቱታዎችን ሲያስተባብል መቆየቱም ይታወቃል።