ሲፒጄ በፍትህ ጋዜጣ ላይ የተጣለውን እገዳ ኮነነ

ሐምሌ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ተቀማጭነቱ ኒውዮርክ የሆነው አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ድርጅት ( ሲፒጄ) በፍትህ ጋዜጣ ላይ የተጣለው እገዳ በኢትዮጵያው ውስጥ የሚታየው አፈና የደረሰበትን ደረጃ ያሳያል ብሎአል።

የሲፒጄ የምስራቅ አፍሪካ ዋና አማካሪ የሆኑት ቶም ሮድስ እንደተናገሩት ” የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ህመም በተመለከተ ምን ነገር እንዲነገርባቸው አይፈልጉም፣ ይህም በአገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋውን የአፈና መጠን በገሀድ የሚያሳይ ነው።”

ማንኛውም ዜጋ የመሪውን ጤንነት በተመለከተ እውነተኛውን መረጃ የማግኘት መብት አለው አሉት ቶም ሮድስ፣ የመንግስት ባለስልጣናትም ውሳኔያቸውን ቀልብሰው ጋዜጣው እንደገና እንዲታተም እንዲፈቅዱ ጠይቀዋል።

መንግስት ጋዜጣው እንዳይታተም ያገደው ለብሄራዊ ጸጥታ አደገኛ የሆነ መረጃ ይዟል በሚል ሰበብ ነው። ይሁን እንጅ ጋዜጣው በአቶ መለስ የጤና ሁኔታ ከተለያዩ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን ያሰባሰባቸውን መረጃዎች በፊት ገጡ ይዞ ለመውጣት አቅዶ እንደነበር ነው ሲፒጄ የገለጠው።

ዛሬ የጋዜጣው አዘጋጆች ከጠበቃቸው ጋር በመሆን የፍትህ ሚኒስትር ባለስልጣናትን ለማነጋገር ሙከራ ቢያደርጉም፣ ሚኒስቴሩ መረጃ የለኝም በማለት መልሶአቸዋል።

አቃቢ ህግ ጋዜጣው የታገደበትን ምክንያት በ48 ሰአታት ውስጥ ለፍርድ ቤት ማቅረብና ክስ መመስረት ቢኖርበትም፣ እስካሁን ድረስ ከፍርድ ቤት የተላከ ደብዳቤ አለመኖሩን ነው ለማወቅ የተቻለው።

በሌላ ዜና ደግሞ የአቶ መለስ ዜናዊ የጤንነት ሁኔታ ለብዙዎች እንቆቅልሽ እንደሆነ ቀጥሎአል። መንግስት ትክክለኛውን መረጃ ለማውጣት ፈቃደኛ አለመሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ አርፈዋል ወይም በማይድን በሽታ ተይዘዋል የሚለው ወሬ በስፋት እንዲሰራጭ አድርጎታል።

የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኞች ትክክለኛውን መረጃ ለማግኘት ላይ ታች ቢሉም እስካሁን ድረስ አልተሳካላቸውም።

የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት እንደሚሉት አቶ መለስ ቢድኑ እንኳ ወደ ስራ የመመለስ እድላቸው የመነመነ ነው።

ገዢው ፓርቲ የአቶ መለስ የጤና ሁኔታ ይፋ ከሆነ አገር አይረጋጋም በሚል እሳቤ ዜናውን ይፋ ከማድረግ እንደተቆጠበ  የቅርብ ምንጮች ይናገራሉ። ይሁን እንጅ በተቃራኒው በመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች እና በጸጥታ አስከባሪዎች የሚታየው አለመረጋጋት ከታሰበው ይልቅ ተቃራኒ ውጤት እያመጣ መሆኑን ነው ምንጮቹ የሚጠቁሙት።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide