ሱዳኖች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመግባት ጥቃት ፈጸሙ

ሱዳኖች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመግባት ጥቃት ፈጸሙ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 26 ቀን 2010 ዓ/ም) በቋራ ወረዳ በነፍስ ገበያ አካባቢ ከሱዳን ወታደሮች ጋር እየተካሄደው ባለው ውጊያ እስካሁን 7 የሱዳን ወታደሮች ተገድለው 2 ሙሉ የጦር መሳሪያዎችን የታጠቁ መኪኖች ተማርከዋል። ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ከሶስት ቀናት በፊት በተጀመረው ጦርነት የተወሰኑ አርሶአደሮች መጎዳታቸውንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ሱዳን በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ጥቃት ስትፈጽም ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ጥቃት ከመፈጸሙ ከአንድ ሳምንት በፊት ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው ጥቃቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ ጥረት እያደረጉ ያሉ የህወሃት ቡድኖች ከሱዳን የጦር አዛዦች ጋር በመሆን በጋራ ያቀናበሩት ነው። የጦርነቱ አላማ የክልሉን አስተዳደር በጦርነት ፋታ በመንሳት፣ አሁን ያለው አስተዳደር በለውጡ ጥያቄዎች ዙሪያ ትኩረት እንዳያደርግ አቅጣጫ ማስቀየር እንዲሁም ክልሉ እንዳይረጋጋ በማድረግ ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር የታለመ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ።
ህወሃት በአካባቢው ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ወስደው የሚሰሩ የህወሃት ጄኔራሎችን መጠቀሙን ምንጮች ይናገራሉ።
ሱዳን ከፍተኛ የሆነ ጦር ወደ ድንበር እያስጠጋች መሆኑን ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም ወረራውን ለመመከት ወደ ድንበር ተንቀሳቅሷል። እስካሁን ድረስ የአካበባው ህዝብና ሚሊሺያዎች የሱዳንን ጥቃት ሲመክቱ ቆይተዋል።
በሌላ በኩል ከ3 ቀናት በፊት የህወሃት የልኡካን ቡድን በሚስጢር ወደ ካርቱም ሄዶ ከሱዳን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ተነጋግሯል። የልኡካን ቡድኑን ተልእኮ የመንግስት ባለስልጣናት እንደማያውቁት የገለጹት የደህንነት ምንጮች፣ ትናንት የሱዳንን ድንበር አቋርጠው ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገብተዋል።