ሱዳን የግብጽ የግብርና እና የእንሣት ተዋጽኦ ምርቶች ወደ አገሯ እንዳይገቡ እገዳ ጣለች

ግንቦት ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሱዳን መንግስት የካቢኔ አባላት የግብጽ የግብርና እና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ወደ አገራቸው እንዳይገባ ማገዳቸውን የሱዳን መንግስት ልሳን የሆነው ሱና የዜና አውታር ማክሰኞ እለት ዘገቧል። ካቢኔው አክሎም በቀጥታ ከጎረቤት ግብጽ በኩል ወደ ሱዳን የሚገቡ ማንኛውንም ምርቶች እንዳያስገቡ ለግል ባለሃብቶችም ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
በሱዳን እና በግብጽ መሃከል የተነሳው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ የመጣ ሲሆን ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የሱዳን መንግስት የግብጽ የግብርና ሸቀጦች ላይ ማእቀብ መጣሉ ይታወሳል። የግብጽ መንግስት የሱዳን ተቃዋሚዎችን ጥቃት ማገዙን ተከትሎ ፕሬዚዳንት አልበሽር በመቃወማቸው የሱዳን ጠቅላይሚንስትር የግብጽ ጉብኝታቸውን ሰርዘዋል። ባለፈው ሳምንት የሱዳን ወታደራዊ ባለስልጣናት የግብጽ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችn በደቡባዊ ዳርፉር በተደረገ ውጊያ መማረካቸውን አስታውቀዋል። የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በበኩላቸው የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።
የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፋታህ አልሲሲ በበኩላቸው ‘’ግብጽ በማንም አገር ላይ ጉዳይ ታልቃ አትገባም ‘በጎረቤት ወንድም አገር ሱዳን ላይ እንዴት ጥቃት እንፈጽማለን? እኛ በመከባበር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ እንከትላለን።’’ ብለዋል።
የግብጽ መንግስት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል ሱዳን ላይ ማእቀብ እንዲጣል ቅስቀሳ ታደርጋለች ሲል የሱዳን መንግስት ክስ ያቀርባል። የግብጽ መንግስት በበኩሉ የግብጽን ጥቅም በሚጻረር ሁኔታ በዓባይ ግድብ ግንባታ ላይ የሱዳን መንግስት ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፍዋል በማለት ቅሬታ ማቅረባቸውን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።