ግንቦት ፲፮ ( አሥራ ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር በዳርፉር አካባቢ ሰሞኑን በተደረገው ጦርነት የሱዳን ጦር ሃይል የግብጽን ተሽከርካሪዎችና ታንከሮች ከአማጽያኑ እጅ ላይ መማረኩን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት አልበሽር “ በዙሪያችን ያሉ አገራት እየፈራረሱ ነው፣ ጦራቸውም እየፈራረሰ ነው፣ ነገር ግን የሱዳን መከላከያ ሰራዊት የቱንም ያክል ሴራ እና ተንኮል ይሸረብበት፣ አሁንም በጥንካሬ ዘልቋል።” ብለዋል።
የሱዳን ጦር ሃይል አስገራሚ ድል ተቀዳጅቷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በሊቢያና በደቡብ ሱዳን በኩል የገቡትን የዳርፉር አማጽያን በሁለት ቀናት ጦርነት ደምስሷቸዋል ሲሉ አክለዋል።
በደቡብ ሱዳን በኩል ከገቡት 64 ተሽከርካሪዎች ውስጥ 59ኙ መደምሰሳቸውንም የሱዳን ሚዲያ ሴንተር ዘግቧል።
ሱዳን ከህወሃት/ኢህአዴግ ጋር አዲስ የሆነ ወታደራዊ ግንኙነት በመመስረት በሁለቱ አገራት የድንበር አዋሳኝ ቦታዎች ላይ የጋራ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናት።
በተቃራኒው ኤርትራና ግብጽ የጀመሩት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን የኤርትራው መሪ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ለአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። ደቡብ ሱዳን እስካሁን ከሁሉም ጎረቤት አገራት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላት ብትገልጽም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከግብጽ ጋር ከፍተኛ መቀራረብ እያሳየች ነው።
የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ፣ ግብጽና ኤርትራ በመገንባት ላይ ባለው አባይ ግድብ ላይ እያሴሩብኝ ነው ሲል ክስ ያሰማል። ግብጽ በበኩሏ ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ከጎኔ ትቆማለች ብላ ብትጠብቅም፣ ሱዳን ከኢህአዴግ ጎን መቆሙን መርጣለች። በተለይ በርካታ የኢትዮጵያ የመከላከያ አባላት በዳርፉርና በአብየ ግዛት መሰማራታቸው እንዲሁም የኢህአዴግ ባለስልጣናት ለሱዳን ጥያቄዎች ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩ መሆናቸው፣ ሱዳን ከኢህአዴግ ጋር ግንኙነቷን እንድታጠናክር አድርገቷል የሚሉ አስተያየቶች ይሰማሉ።
የህወሃት አገዛዝ በበኩሉ ሱዳን አገዛዙን ለሚቃወሙ ሃይሎች መንቀሳቀሻ ቦታ እንዳትሰጥ ለማድረግ የሱዳንን ጥያቄዎች፣ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ ቢሆንም እየመለሰ ነው።