ኢሳት (ታህሳስ 26 ፥ 2008)
ኢትዮጵያና ግብፅ ባለፈው ሳምንት በሱዳን በተፈራረሙት ስምምነት አተገባበር ዙሪያ የሚመክር ውይይት ረቡዕ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የግብፅ ባለስልጣናት ማክሰኞ አስታወቁ።
ለሁለት ቀን በሚቆየው በዚሁ አስቸኳይ የውይይት መድረክ ግብፅ ያቀረበቻቸው አዳዲስ ሃሳቦች እንዴት ወደተግባር ሊለወጡ እንደሚችሉ የሚመክር መሆኑንም የግብፅ የመስኖ ሚኒስትር ገልጸዋል።
የሃገሪቱ የመስኖ ልማት ሚኒስትር አማካሪ የሆኑት አላ ያሲን ሃገራቸው የወንዙን ፍሰት እንዳታስተጓጉል የሚያደርጉ ሃሳቦችን አቅርባ በተፈጻሚነቱ ዙሪያ ለመምከር ባለሙያዎችን ወደአዲስ አበባ መላኳን እንዳስታወቁ ዘ-ካይሮ ፖስት ጋዜጣ ዘግቧል።
በካርቱም በተፈጸመው ስምምነት ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በተናጥል በግድቡ ላይ ምንም አይነት ስራ እንዳይከናወን ስምምነት መደረሱን የግብፅ ባለስልጣናት ሲገልጹ ቆይተዋል።
በዚሁ በባለ ብዙ አንቀጽ ስምምነት ግድቡን በውሃ የመሙላቱ ሂደት በግድቡ ላይ የሚደረግ ጥናት እስኪጠናቀቅ ድረስ እንዳይከናወን ውሳኔ መደረሱን የግብፅ የመስኖ ልማት ሚኒስትር ሆሳም ሞግሃዚ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ረቡዕ በአዲስ አበባ የሚካሄደው የውይይት መድረክም ግብፅ ያቀረበቻቸው ሃሳቦችና የፈረመቻቸውን ስምምነቶች የሚመረምር እንደሆነም ለመረዳት ተችሏል።
የግብፅ ፕሬዚዳንትና ሌሎች ባለስልጣናት በተፈረመው ስምምነት ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ቢሰጡም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በካርቱም የተደረሰ ምንም አይነት ስምምነት የለም ሲሉ ማስተባበላቸው ይታወሳል።
በተደረሰው የካርቱም የድርድር ውጤት ደስተኛ መሆናቸውን በመግለፅ ላይ የሚገኙት የሃገሪቱ ሃላፊዎች ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ጥቅም አሳልፋ እንዳማትሰጥ አስታውቀዋል።
ለአራት አመት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያና የግብፅ ድርድር ይግባኝ የሌለው የአጥኚዎች ቡድን ውጤት ፍጻሜ ያገኛል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች በግድቡ ላይ የሚያደርጉትን ጥናት በቀጣዩ ወር ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።