ኢሳት (ግንቦት 1 ፥ 2008)
የግብጽ እና የሱዳን መንግስታት ይገባኛል የሚያነሱባቸው ሶስት የድንበር መንደሮች በአባይ ግድብ ድርድር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን የግብፅ ባለስልጣናት ይፋ አደረጉ።
የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አል-በሽር ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉ ጊዜ ግድቡ ሱዳንና ኢትዮጵያን የሚጠቅም ነው ሲሉ የሰጡት መግለጫ በግብፅ ዘንድ ቅሬታን መቀስቀሱንም አል-ሞኒተር የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
ሱዳንና ግብፅ በጋራ ድንበሮቻቸው ዙሪያ በሚገኙት የሃላየብ እና የሻላተን መንደሮች ላይ የይገባኛል ጥያቄን የሚያነሱ ሲሆን፣ የሱዳን መንግስት የመንደሮቹ እጣ ፋንታ መፍትሄ እንዲያገኝ ለግብፅ ባለስልጣናት ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል።
ይሁንና፣ ሱዳን በአባይ ግድብ ግንባታ ላይ ያላት አቋም ባቀረበችው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ላይ ጥርጣሬን እንዳሳደረ አል-ሞኒተር ጋዜጣ የግብፅ ባለስልጣናትን ዋቢ በማድረግ በዘገባው አስፍሯል።
የሃላየብና የሻላተን መንደሮች በአሁኑ ወቅት በግብፅ ፖለቲካዊ አስተዳደር ውስጥ ቢገኙም ሱዳን የይገባኛል ጥያቄ እንዳላት ጋዜጣው አስነብቧል።
ይሁንና፣ ሱዳን በአባይ ግድብ ላይ እየያዘች የመጣችው አቋም ሁለቱን ሃገራት ወደ አለመግባባት ውስጥ ኣየከተታቸው የሚገኝ ሲሆን፣ በአባይ ግድብ ላይ እየያዘች የመጣችው አቋም ሁለቱን ሃገራት ወደ አለመግባባት ውስጥ እየከተታቸው የሚገኝ ሲሆን በአባይ ግድብ ላይ ሲካሄድ የቆየው ድርድርም መጓተት እንዲያሳይ ማድረጉን ሞና ኦማር የተባሉ የግብፅ ባለስልጣን ለአል-ሞኒተር ጋዜጣ ገልጸዋል።
ሶስቱ ሃገራት የአባይ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ለማስጠናት ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች ቢመርጡም በሱዳንና በግብፅ መካከል የተነሳው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ኩባንያዎች ወደ ስራ እንዳይገቡ ማድረጉንም ለመረዳት ተችሏል።
በግብፅ ላይ የሚካሄደው ጥናት መዘግየትም የአባይ ግድብ ድርድር ያለውጤት እንዲያበቃ ሊያደርግ የሚችል አልያም ግብፅ ራሷን ከድርድር እንድታግድ የሚያደርግ እንቅስቃሴ እንደሆነ አልሞኒተር በጋዜጣ ዘገባው አመልክቷል።
በግብፅና ሱዳን መካከል የተነሳን የድንበር ጥያቄ ተከትሎም በኢትዮጵያና ግብፅ መካከል ሲካሄድ የነበረ የአባይ ግድብ ድርድር ለወራት ያህል መስተጓጎሉ ታውቋል።
ከግብፅ ጋር የድንበር ጥያቄን አንስታ የምትገኘው ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋርም ተመሳሳይ ጥያቄን አንስታ የምትገኝ ሲሆን፣ የሁለቱ ሃገራት ድንበር በቅርቡ ይካለላል ሲሉ የሱዳን ባለስልጣናት በመግለጽ ላይ ናቸው።
ይሁንና የኢትዮጵያ ታሪክ ምሁራንና የተለያዩ የህብረትሰብ ክፍሎች እርምጃውን የኢትዮጵያ ጥቅም የሚጎዳ ነው በማለት ተቃውሞን አቅርበዋል።