ኢሳት (ግንቦት 3 ፥ 2008)
መንግስት ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ብድርን በማሰባሰብ ሰባት የስኳር ፋብሪካዎችን ለመገንባት የነደፈው እቅድ ለስደስት አመት ያህል ጊዜ ወደ ተግባር ባለመለወጡ ከፍተኛ ኪሳራ ማስከተሉ ተገለጠ።
የስኳር ፋብሪካዎቹን ግንባታ እንዲቆጣጠር ሃላፊነት የተሰጠው የስኳር ኮሮፖሬሽን በበኩሉ ለእቅዱ አለመሳካት ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን ተጠያቂ ማድረጉ ታዉቋል።
ሰባቱ የስኳር ፋብሪካዎችን ለመገንባት መንግስት ከአባዳሪ አባላት ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የወሰደ ሲሆን ቀሪዎቹን ደግሞ ከሃገር ውስጥ ባንኮች መውሰዱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ይሁንና፣ ለፋብሪካዎቹ ግንባታ ወደ 77 ቢሊዮን ብር ተመድቦ ከስድስት አመት በፊት እንቅስቃሴ ቢጀመርም አንድም ፋብሪካ ወደ ስራ ሳይገባ መቅረቱን ሰሞኑን ለፓርላማ ሪፖርትን የቀረበው የስኳር ኮርፖሬሽን ገልጿል።
የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ፋብሪካዎችን ለመገንባት ስምምነት ፈጽሞ አብዛኛውን ክፍያ ቢወስድም የፋብሪካዎቹን ግንባታ ግን ማጠናቀቅ ሳይችል መቅረቱን ለኮርፖሬሽኑ በቅርቡ በሃጋላፊነት የተመደቡት አቶ እንግዳወርቅ አብቴና ሌሎች ሃላፊዎች ለፓርላማ አስረድተዋል።
የፓርላማ አባላት በበኩላቸው ስራው ባልተሰራበት ወቅት ለብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከ90 በመቶ በላይ ገንዘብ ለምን እንደተከፈለ ጥያቄ ማቅረባቸውም ታውቋል። ግንኙነቱ በቢዝነስ ህግ የማይገዛ መሆኑን፣ እንዲሁም ሃላፊዎቹ ዕውነቱ እንዳይገለጽ ማሸማቀቃቸውን ከሃላፊዎች ገለጻ መረዳት ተችሏል።
የስኳር ፋብሪካዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃሉ በሚል የሸንኮራ አገዳ ልማት ቢካሄድም ምርቱ ያለምንም አገልግሎት ለብልሽት መዳረጉንም ከሃገር ቤት ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል። አገዳውን ለማስወገድም ለከፍተኛ ወጭ መዳረጋቸውንም አመልክተዋል።
ከወራት በፊት የስኳር ኮርፖሬሽን በቢሊዮን የሚቆጠር ኪሳራ ደርሶበት እንደነበር የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምንጮች ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአቶ አባይ ጸሃዬ ስር ይተዳደር የነበረው የስኳር ኮርፖሬሽን ሃገሪቱን ስኳር ላኪ ሃገር በማድረግ በየአመቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢን ያስገኛል ተብሎ የነበረ ሲሆን፣ የእቅዱ አለመሳካትን ተከትሎም መንግስት በተያዘው በጀት አመት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላርን በመመደብ የስኳር ግዢን እያከናወነ ይገኛል።
ኮርፖሬሽኑ እያቀረበ ያለውን ቅሬታ በተመለከተ የመንግስት ባለስልጣናት በይፋ የሰጡት ምላሽ አለመኖሩንም ታውቋል።