ኢሳት ሰበር ዜና ዓርብ ሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም፡- በኢህአዴግ መንግሥትና በኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ የተፈጠረው መቃቃር ወደ አጠቃላይ አካላዊ ግጭት አመራ፡፡ ዛሬ ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ጀምሮ በአወሊያ መስኪድ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ለእሁድ አጠቃላይ የአንድነትና የድምፃችን ይሰማ ተቃውሞ ዝግጅት በማድረግ ላይ በሚገኙ ሙስሊሞች ላይ የፌዴራል ፖሊስ ቅጥር ጊቢውን ጥሶ በመግባት ሙስሊም ማህበረሰቡን በቆመጥ በአስለቃሽ ጭስ በመደብደብና መሳሪያ ወደ ላይ እና ወደ ሰው በመተኮስ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡
በአወሊያ መስኪድ የሚገኙ ሙስሊሞች በጩኸት የድረሱልን ድምጽ በማሰማታቸው በመጀመሪያ በአካባቢው የሚገኙ ሙስሊምና ክርስቲያን ዜጎች /ይበልጡኑ ወንዶች/ ከውጪ ተደራጅቶ በገባው ፖሊስ ላይ ድንጋይ በመወርወር ከውስጥ ያሉትን ሙስሊሞች በመታደግ ላይ ይገኛሉ፡፡ሁኔታውን ሙስሊሙ እና ክርስቲያኑ ማህበረሰብ በስልክ በመነጋገር በየአካባቢው በሚገኙ መስኪዶች በመሰባሰብ የጩኸት ድምጽ ያሰሙ ሲሆን በየመሰኪዱ የሚገኙ ኢማሞች የአስቸካይ የአደጋ ጊዜ አዛን ድምጽ በማሰማታቸው ሙስሊሙ በመላ ከቤቱ እየወጣ በየመስኪዱ በመሰባሰብ ወደ አወሊያ በማምራት ከፖሊስ ጋር በድንጋይ ውርወራ በመጋጨት ላይ ይገኛሉ፡፡
ከመርካቶ አንዋር መስኪድ፣ ከአዲሱ ሚካኤል አቅራቢያ ከሚገኘው መስኪድ፣ ከኮልፌ፣ ከወይራ ሰፈር እና ከተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በርካታ ሙስሊሞች ወደ አወሊያ መስኪድ በማምራት ላይ ሳሉ በየመንገዱ በሽፍን የፖሊስ ሚኪና ቆርጠው ሊያስቀሯቸው ከሚሞክሩ የፖሊስ አባላት ጋር በድንጋይ በነመጋጨት ላይ ይገኛሉ፡፡ አወሊያ መስኪድ መድረስ የቻሉት ስብስቦችም ከፖሊስ ጋር በመጋጨትና ወደ አወሊያ ገብተው ለመቀላቀል እየሞከሩ ነው፡፡
አወሊያ ውስጥ መግባት ሳይችል ከፖሊስ ጋር በድንጋይ በመጋጨት ላይ ያለው ከማል የተባለ ሰው በቦታው ሆኖ ለዘጋቢያችን በሥልክ እንዳሰማው አላህ ኡ አክበር፣ የሚሉ በርካታ ሙስሊሞች ድምጽ እና የድንጋይ፣ የአስለቃሽ ጢስ እና የመሳሪያ ተኩስ ድምጽ በቀጥታ ያሰማው ሲሆን በመሣሪያ የተመቱ ሰዎች እንዳሉ መስማቱንና በርካታ ሰዎች በአስለቃሽ ጢስ የተጉዱ፣ በዱላ የተቀጠቀጡ የተፈነከቱ ሰዎችን ማየቱን ገልፆ ከእርሱ በፊት በቦታው የደረሱ ሙስሊሞች እንደነገሩት በርካታ ሰዎች በፖሊስ መኪና እየተጫኑ መሄዳቸውን እንደነገሩት ገልፆል፡፡
ከምሽቱ ስድስት ሰዓት ላይ በኮንትራት ታክሲ በመውጣት ሁኔታውን ለመከታተል የሞከረው ዘጋቢያችን መርካቶ በሚገኘው በአንዋር መስኪድ፣ ፒያሳ በሚገኘው በኒ /ኑር/ መስኪድ እና አዲሱ ሚካኤል አቅራቢያ በሚገኘው መስኪድ ዙሪያ እና አካባቢ በርካታ ሙስሊሞችና ክርስቲያን ወጣቶች፣ ጎልማሶችና ሽማግሌዎች እየተሰባሰቡ ወደ አወሊያ ለመሄድ ሲንቀሳቀሱ የተመለከተ ሲሆን ጉዙውን ወደ አወሊያ ቢቀጥልም በፖሊስ ብዛት የተደናገጠው የታክሲ ሾፌር ወደ ኋለ፤ በመመለሱ ከዊንጌት ትምህርት ቤት ማለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ዕረቡ ዕለት የመንግሥት የደህንነት ኃይሎች ሁለት የሙስሊም ተወካዮችን አግተው የእሁዱን ተቃውሞ ካላቋረጡ እንደሚገሏቸው በመንገር ማስፈራራታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡