ሰሜን ኮሪያ እያደረገች ባለችው የኒዩክለው ሙከራ ህጻናትና የአካባቢው ነዋሪዎች እየተጎዱ ነው ተባለ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 28/2010)ሰሜን ኮሪያ እያደረገች ባለችው የኒዩክለው ሙከራ ሳቢያ በሚፈጠረው አደገኛ መርዝ ያልተስተካከለ ሰውነት ያላቸው ሕጻናት እንደሚወለዱና በሕይወት መቆየትም እንደማይችሉ አንድ የምርምር ተቋም ይፋ አደረገ።

ከሰሜን ኮሪያ ከድተው ወደ ደቡብ ኮሪያ የሄዱ ሰዎች ለምርምር ተቋሙ እንደገለጹት ወደ ስድስት ከሚደርሱና የኒዩክለር የሙከራ ፍንዳታ ከሚደረግባቸው አካባቢዎች ከሚመነጭ ወንዝ የሚመጣውን ውሃ ነዋሪዎች ይጠቀሙታል።

ይህ ደግሞ ለህጻናቱ የአካል አለመስተካከልም ሆነ የሟቾች ቁጥርን ለመጨመር ምክንያት ሳይሆን አልቀረም ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ከሰሜን ኮሪያ ከድተው ወደ ደቡብ ኮሪያ የሄዱ ከ20 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለአንድ የምርምር ተቋም እንደተናገሩት ኪልጁ በመባል በሚጠራው የሰሜን ኮሪያ የኒዩክለር መሞከሪያ ቦታ አቅራቢያ የሚወለዱ ሕጻናት የሰውነት አካላቸው ያልተስተካከለ መሆንና በአካባቢውም የሞት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ምክንያቱ በኒዩክለር ሙከራ ሳቢያ በተፈጠረው አደገኛ ጨረር አማካኝነት ሳይሆን እንዳልቀረ ስጋታቸውን ተናግረዋል።

የተወለዱ ሕጻናትም ማደግ እንዳልቻሉ ራዕይ ለሰሜን ኮሪያ የተባለን የምርምር ተቋም ጠቅሶ አንድ የደቡብ ኮሪያ ጋዜጣ ይፋ አድርጓል።

ሀገሪቱን በመክዳት ወደ ደቡብ ኮሪያ የመጡት እነዚህ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነም ወደ ስድስት ከሚደርሱና የኒዩክለር የሙከራ ፍንዳታ ከሚደረግባቸው አካባቢዎች ከሚመነጭ ወንዝ የሚመጣውን ውሃ ነዋሪዎች ይጠቀሙታል።

ምንም አይነት ማስጠንቀቂያም ሆነ የጥንቃቄ ርምጃ በመንግስት እንደማይሰጥ ጠቅሰዋል።

አንደኛው ምስክር እንደተናገረውም ሙከራው ከመደረጉ ቀደም ብሎ መንግስት ወታደሮቹን ብቻ ከአካባቢው ሲያስወጣ ሌሎች ነዋሪዎች ግን ለአደጋው ተጋልጠዋል ብሏል።

ሌላኛው ምስክር እንደሚለው ደግሞ በአካባቢው በሚገኝ ወንዝ አካላቸው የተጎዳ ሰዎች አስከሬን ሲንሳፈፍ ማየቱን ተናግሯል።

የሀገራቸው መንግስት የአካባቢውን ሰዎች ለኒዩክለር ሙከራው የሚሆን ጥልቅ ጉዳጓድ ያስቆፍራቸዋል ሲልም ሁኔታውን አጋልጧል።

በአካባቢው 80 በመቶ የሚሆኑ እጽዋት እንደጠፉም ምስክሮቹ ጨምረው ተናግረዋል።

የሰሜን ኮሪያ መንግስት ሙከራ ከሚያደረግበት ኪልጁ ከተባለው አካባቢ ለሕክምና ወደ መዲናይቱ የሚጓዙ ነዋሪዎች ፒዮንግያንግ ለመግባት እንደማይፈቀድላቸውና ከአካባቢው ለመውጣት የሚሞክሩትም ተይዘው እንደሚታሰሩ ገልጸዋል።

የኒዩክለር ሙከራ በሚደረግበት አካባቢ የሚገኝ የዋሻ መተላለፊያ ባለፈው ወር በመደርመሱ 200 ያህል ሰዎች ሞተዋል ሲል የደቡብ ኮሪያ ቴሌቪዥን ያቀረበውን ዘገባ የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት ውሸት ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

የዘርፉ ተመራማሪዎች ባለፈው ወር ሰሜን ኮሪያ ያደረገችው የሃይድሮጅን ቦምብ 6ኛ የሙከራ ፍንዳታ በአካባቢው ላይ ትልቅ ጉዳት ማድረሱን የሳተላይት ምስሎች ማሳየታቸውን ተናግረዋል።

ከፍንዳታው አካባቢ የሚወጣው ጨረርም የአካባቢው ሀገራትንም ጭምር የሚያሰጋ ጉዳይ እንደሆነ ተመራማሪዎቹ አሳስበዋል።

ሰሜን ኮሪያ እስካሁን ለ6ኛ ጊዜ የኒዩክለው ሙከራ ስታካሂድ ድርጊቱ በተለይ ከአሜሪካ መንግስት ጋር ትልቅ እሰጥ አገባ ውስጥ እንደከተታት አይዘነጋም።

በኢሲያ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትላንት በደቡብ ኮሪያ በጉብኝት ላይ ነበሩ።

ይህን ተከትሎም የሰሜን ኮሪያው መንግስት የዜና አውታር ሰዎችን በማጭበርበር ሀብት ያካበቱት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሁን ከሰሜን ኮሪያ ጋር የኒዩክለር ቁማር ውስጥ ገብተዋል ሲል ዘገባውን አቅርቧል።