ኢሳት (ኅዳር 28 ፥ 2009)
የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ንብረት የሆነው ሰላም ባስ በኦሮሚያ ክልል በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ የ8.5 ሚሊዮን ብር ማጣቱን ገለጸ። በጎንደር በተነሳውና በአማራ ክልል ከተስፋፋው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የደረሰበትን ኪሳራ ይፋ አላደረገም።
አዲስ ፎርቹን ሳምንታዊ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ሰላም ባስን በመጥቀስ ባቀረበው ዘገባ እንደተመለከተው ባለፈው አመት ወደ ነቀምትና አሶሳ የሚያደርገው ጉዞ በመስተጓጎሉ 650 ምልልሶች ተሰርዘዋል። በዚህም የ8.5 ሚሊዮን ብር አጥቷል።
በአማራ ክልል ከተነሳው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በደረሰው ጥቃትና የጉዞ መሰረዝ ስለደረሰው ኪሳራ የተገለጸ ነገር ባይኖርም፣ ከሃምሌ 2008 እስከ ህዳር 2009 ወደ ጎንደር ይደረግ የነበረው ጉዞ ተቋርጦ መቆየቱም በአዲስ ፎርቹን ዘገባ ተመልክቷል። የአውቶቡስ አገልግሎቱ የጎንደር ጽ/ቤትም ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ ተዘግቶ መሰንበቱንም መረዳት ተችሏል።
የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ /ህወሃት/ ንብረት የሆነው ሰላም ባስ ከጎንደሩ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በጎንደር ከተማ ውስጥ በህዝብ መቃጠሉ ሲታወስ፣ ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች ጥቃት እደተሰነዘረባቸውም ማስታወስ ተችሏል።
በነቀምት፣ በሬዳዋ በወሊሶ ጥቃት የደረሰበት ሰላም ባስ፣ በጥቃቶቹ ሳቢያ ሲያስተጓጉል ከመቆየቱም ባሻገር በኦሮሚያ ክልልም መቃጠሉ አይዘነጋም።
በኢትዮጵያ የአውቶቡስ ትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጠው ድርጅቶች ትልቁና 60 ያህል አውቶቡሶች ያሉት ሰላም ባስ፣ ስልጣን ላይ ያለው ቡድን መንግስታዊ ስልጣኑ ተጠቅሞ የሚያደርግለት ልዩ ዕገዛና ድጋፍ እንዲሁም ከባንክ ያለአግባብ በሚወስድ ገንዘብ መስፋፋቱ ሲገልፅ ቆይቷል።