የካቲት ፲፭ ( አሥራ አምስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባሳለፍነው ሳምንት ሱዳን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመገኘት በሰላማዊ መንገድ ሕጋዊ መብቶቻቸውን የጠየቁ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ በኤንባሲው ፈቃጅነት በሱዳን የጻጥታ ኃይሎች ድብደባ፣ የጅምላ እስራት፣ አካላዊ ጥቃቶች መፈጸሙ እና አንድ ስደተኛም በስለት ተወግተው መገደላቸው ይታወቃል::
በሱዳን የፀጥታ ሃይሎች ተይዘው በተጨናነቀ በእስር ቤት ታጉረው የተለያዩ ሰቆቃ ሲፈፀምባቸው ከነበሩት ስደተኞች ውስጥ የአመጹ መሪ አስተባባሪ የተባሉትን በመለየት የሱዳን መንግስት ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው እንዲሰጡ አድርጓል። ቁጥራቸው 63 የሚሆኑት እነዚህ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች እስካሁን በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ማወቅ አልተቻለም።
በሌላ በኩል ታንዛኒያ በሕገወጥ መንገድ ወደ አገሬ ገብተዋል ያለቻቸውን 13 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በቁጥጥር ስር አዋለች
በታንዛኒያ የኪሊማንጃሮ ግዛት ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ዊብሮድ ሙታፉንጋ ሕገወጦቹ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ትክክለኛ የሆነ ማንነታቸውን የሚገልጽ ሕጋዊ ሰነድ አለመያዛቸውን ጠቅሰው በኬኒያ እና ታንዛኒያ ድንበር አቅራቢያ አዲስ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ እንደሚገነባ ተናግረዋል። ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞቹ የአገሪቱ ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ ሰኞ እለት በሚዋንጋ አውራጃ ሚኖያ መንደር ውስጥ በጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። በታንዛኒያ ውስጥ ለመኖር የሚያስችል ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች ወደ በአገራችን ገብተው እንዲኖሩ አንፈቅድም ሲሉ የፖሊስ አዛዡ ገልጸዋል።
እንደ ኪሊማንጀሮ ግዛት የስደተኞች የስታስቲክ ጽሕፈት ቤት መረጃ ቁጥራቸው ከ259 የሚሆኑ ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ያልያዙ ሕገወጥ ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል።