ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አስባችኋል በሚል ሰበብ ሰላማዊ ዜጎች እየተደበደቡ ነው ተባለ

ኢሳት ዜና (ሃምሌ 16, 2007)

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ወደ አዲስ አበባ ከተማ በሚገቡ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ተንቀሳቅሳችኋል ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች በእስር ቤት ድብደባ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤት ገለጹ።

ሐሙስ እለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት አቶ መርከቡ ሀይሌና አቶ አበበ ቁምላቸው ፕሬዘዳንት ኦባማ ወደ ሀገሪቱ በሚመጡ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ተንቀሳቅሳችኋል ተብለው ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።

ቄራ በሚገኝ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት አቶ አበበ ቁምላቸው ደህንነቶች “ ከሌሎች አባላት ጋር በመሆን ሁከት ለመፍጥር እያሴራችሁ ነው” በሚል ምርመራ እንደሚያደርጉባቸውና ድብደባ እንደሚፈጽሙባቸው ለችሎት ማስረዳታቸውን ከሀገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ጉዳያቸውን የተመለከተ ፍርዱ ቤቱም ለሶስተኛ ጊዜ ለሀምሌ 20/2007 ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን/ፖሊስ ምርመራ እያካሄደ እንደሆነ ለችሎት ገልጿል።

በተመሳሳይ ሁኔታ አራዳ ፍርድ ቤት በዝግ ችሎት አቶ መርከቡ ሀይሌ ፕሬዘዳንት ባራክ-ኦባማ ወደ አዲስ አበባ በሚገቡ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ተንቀሳቅሳችኋል በሚል ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ ፖሊስ ለችሎት አስረድቷል።

ጉዳዩን የተመለከተ ፍርድ ቤቱም ለሀምሌ 20/2007 ተመሳሳይ ቀጠሮን መስጠቱ ታውቋል።

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ባራክ-ኦባማ በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉብኝት ተከትሎ በአዲስ አበባ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሀይል ተሰማርቶ መገኘቱን ነዋሪዎች በመግለጽ ላይ ናቸው።

በከተማዋ ምንም አይነት ህዝባዊ ስብሰባዎችን በማስቆም ፍተሻን እያካሄዱ ነዋሪዎች ገጸዋል። ፕሬዘዳንት ኦባማ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን ጨምሮ ከአፍሪካ ህብረት ሀላፊዎች ጋር ውይይት ያካሂዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።