ሬክስ ቴሊርሰን ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 23/2010)

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቴሊርሰን በመጭው ሳምንት ኢትዮጵያን ጨምሮ 5 የአፍሪካ ሀገራትን እንደሚጎበኙ ተገለጸ።

ሬክስ ቴሊርሰን በመጭው ረቡዕ ወደ ኢትዮጵያ በማምራት በሃገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ዙሪያ ከሕወሃት/ኢሕአዴግ ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ ትብሏል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሬክ ቴሊርሰን ወደ አፍሪካ የሚያቀኑት ስልጣን ከያዙ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በዚሁም ጉዟቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ ቻድን፣ጅቡቲን፣ኬንያንና ናይጄሪያን ይጎበኛሉ ነው የተባለው።

በኢትዮጵያ ቆይታቸውም ከሕወሃት/ኢሕአዴግ ባለስልጣናትና ከአፍሪካ ሕብረት የስራ ሃላፊዎች ጋር እንደሚመክሩም ታውቋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክ ቴለርሰን ወደ ኢትዮጵያ ማምራታቸው ዩናይትድ ስቴትስ የሃገሪቱ ችግር ያሳሰባት መሆኑን ያመለክታል ተብሏል።

አሜሪካ የኢትዮጵያው አገዛዝ የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደማትቀበለው ብትገልጽም ፓርላማው ግን እንዳጸደቀው ለማወቅ ተችሏል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በአምባሳደሩ በኩል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መቃወሙ ይታወሳል።

አሜሪካ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ከማብረድ ይልቅ ሁኔታውን ያባብሰዋል ነው የምትለው።

ኢሳት ከዲፕሎማቲክ ምንጮች ባገኘው መረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሃገሪቱ እንደማይታወጅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ ዋሽንግተን ዲሲ በነበሩ ጊዜ ማረጋገጫ ሰጥተው እንደነበር መግለጻችን ይታወሳል።

ይህ ባለመሆኑም አሜሪካ ወሳኔው እንዳሳዘናት ገልጻ ነበር።

ዶክተር ወርቅነህ አዋጁ ለምን እንደታወጀ አሜሪካ መጥቼ ላስረዳ ቢሉም በኋይት ሃውስ አስተዳደር ጥያቄያቸው ተቀባይነት አላገኘም።

ዶክተር ወርቅነህ በሌላ ስራ አጋጣሚ ኢትዮጵያ የነበሩ የአሜሪካ ዲኦሎማቶችን ለማስረዳት ሰዎቹን ወደ አቶ ስብሃት ነጋ፣አቶ አባይ ጸሃዬና አቶ ስዩም መስፍን እንደወሰዷቸውም መገለጹ ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ዲፕሎማቶቹን አሁን በይፋዊ ስልጣን ላይ ወደ ሌሉ ሰዎች  መውሰዳቸው ሃገሪቱን ከጀርባ የሚያሽከረክሩት ሌሎች መሆናቸውን አመላካች ነው ተብሏል።