(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 17 2010) ሩሲያ ውስጥ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ 64 ያህል ሰዎች ሕይወታችው አለፈ።
10 ያህል ሰዎች ደግሞ እስካሁን የገቡበት አልታወቀም።
ከሟቾቹ ውስጥ ብዙዎቹ ሕጻናት መሆናቸው ተመልክቷል።
በሩሲያ ኬሞሮቭ በተባለው ከተማ በአንድ የገበያ እና የመዝናኛ ማዕከል በተነሳው ቃጠሎ 64 ያህል ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።
ከርዕሰ መዲናዋ ሞስኮ 3 ሺሕ 600 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሳይቤሪያ ግዛት በሚገኘው ኬሞሮቮ ከተማ በገበያ እና በመዝናኛ ማዕከል ሕንጻ ላይ ትናንት ዕሁድ በደረሰው ቃጠሎ ከሞቱት 64 ያህል ሰዎች በተጨማሪ 10 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም።
ከሞቱት እና ከተሰወሩት ሰዎች ውስጥ 41ዱ ሕጻናት መሆናቸው ተመልክቷል።
የእሳት ቃጠሎውን ለመግታት እና ሰለባዎቹን ለመታደግ 660 የሚሆኑ የአደጋ ግዜ ሰራተኞች በአካባቢው መሰማራታቸውም ተዘግቧል።
የአደጋው መንስኤ እስካሁን አልታወቀም።