ሞያሌ ኣካባቢ በተነሳው ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች ተገደሉ::

ሐምሌ ፳ (ሀያ)ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ኢሳት የሞያሌ ነዋሪዎችን በስልክ አነጋግሮ ባጠናከረው መረጃ ከሶስት ቀናት በፊት በተነሳው ተቃውሞ ከ20 በላይ ሲቪሎችና 1 የፌደራል ፖሊስ ተገድለዋል። 7 ፖሊሶች ደግሞ በጽኑ ቆስለዋል። ግጭቱ የሶማሊ ብሄረሰብ ተወላጅ በሆኑ ገሪዎችና የኦሮሞ ተወላጅ በሆኑ ቦረናዎች መካከል የተፈጠረ ቢሆንም፣ የሁለቱም ክልል ፖሊሶች ጎራ ለይተው መታኮሳቸውን ነው ነዋሪዎች የሚገልጡት።

ሞያሌ ከተማ በሁለት የክልል መንግስታት የምትተዳደር ከተማ ናት።  የከተማዋ አንደኛው ክፍል በሶማሊ ክልል ስር ሲሆን፣ ሌላኛው ከፍል ደግሞ በኦሮሚያ  ክልል ይተዳዳራል። በከተማዋ ውስጥ ሁለት ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ሁለት አይነት ትምህርት ቤቶችና ሁለት አይነት የትራፊክ ፖሊሶች አሉ።

ሰሞኑን በተነሳው ግጭት የገሪ ፖሊሶችና ታጣቂዎች ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ ጣቢያ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ ፖሊስ ጣቢያውን ለማቃጠል ሞክረው ነበር። ጣቢያው ከቃጠሎ ቢድንም፣ ሁለት ቤቶች መንደዳቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል።

የፌደራል ፖሊስ አባላት ሁለቱን ወገኖች ለመለያየት ሙከራ አድርገው ሲያቅታቸው በሁለቱም ታጣቂዎች ላይ ተኩስ በመክፈት በርካቶችን አቁስለዋል።

ዛሬ ከሰአት በሁዋላ ግጭቱ የረገበ ቢሆንም፣ ህዝቡ ግን ከቤቱ ለመውጣት አልደፈረም። በከተማ ውስጥ አሁንም በብዛት የሚንቀሳቀሱት የፌደራል ፖሊስ አባላት ናቸው።

የፖለቲካ ተንታኞች የሞያሌ ግጭት በዘር ላይ የተመሰረተው የፌደራሊዝም ስርአቱ ውጤት ነው በማለት እንደሚናገሩ ይታወቃል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide