ሞያሌ መረጋጋት አለመቻሉዋን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ
ከከተማዋ የተፈናቀሉት ዜጎች እስካሁን አለመመለሳቸውም ታውቋል
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 25 ቀን 2010 ዓ/ም) የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት የሶማሊ ልዩ ሃይል አባላት በየጊዜው የሚፈጽሙት ግድያ ፣ ነዋሪዎችን አፍኖ የመውሰድ ድርጊት ሊቆም በለመቻሉ እንደ ልባቸው ወጥተው መግባት አልቻሉም።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ አብዛኛው የከተማው ነዋሪዎች ቤታቸውን ዘግተው ለመቀመጥ መገደዳቸውን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ የሶማሊ ልዩ ሃይል አባላት መንገድ ላይ ያገኙትን ሰዎች እያፈኑ በመውሰድ አዳራሻቸውን አጥፍተዋል።
ትናንት ጠዋት ህዝቡ ወደ አደባባይ መውጣት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ ከሰአት በሁዋላ ጸጥታው ተመልሶ መደፍረሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊት 13 የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች በገደሉበት ወቅት ተፈናቅለው ወደ ኬንያ የተሰደዱ ሰዎች ብዙዎቹ አሁንም በድንበር አካባቢ እንደሚገኙና እንዳልተመለሱ ነዋሪዎች ገልጸዋል።