ሟቹ ጠ/ሚር መለስ ዜናዊ ትግራይን የኢንዲስትሪ ማእከል ለማድረግ ጽሁፍ አዘጋጅተው ነበር ተባለ

ጥቅምት ፳፱ (ሀያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ትግራይን የኢንደስትሪ ማእከል ለማድረግ አቶ መለስ ያወጡትን ስትራቴጂ ለመተግበር ርብርብ በማድረግ ላይ መሆኑን ወ/ሮ አዜብ መስፍን ገለፁ። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤትና የ ኤፈርት ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ወ/ሮ አዜብ መስፍን የ ኤፈርት ኩባንያዎች እየተጠናከሩ መምጣታቸውንም ገልፀዋል ።

ከኤፈርት ኩባንያዎች አንዱ ሉሆነው ዋልታኢንፎርሜሽን ማዕከል ወ/ሮ አዜብ መስፍን በሰጡት ቃለ ምልልስ ያቶ መለስ ሕልፈት በኤፈርት ኩባንያዎች ላይ ትንሽ መቀዛቀዝ ያሳየቢሆንም እድገቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተዋል ። መስፍን ኢንጂነሪንግ በሶስት እጥፍ ማደጉንና አሁን ወደ አምስት እጥፍ ለማሳደግ ርብርብ መቀጠሉን ወ/ሮ አዜብ አብራርተዋል ።አልመዳ ጨርቃጨርቅ፣ መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ፣ ሱር ኮንስትራክሽን ጨምሮ ሁሉም የኤፈርት ኩባንያዎች እየተስፋፉና እየተጠናከሩ መሆናቸውን የገለፁት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ኩባንያዎቹ በዚህ አመት ብቻ 1.7 ቢሊየን ብር ትርፍ ለመሰብሰብ የ11.7 ቢሊዮን ብር ዕቃና አገልግሎት ለገበያ እንደሚያቀርቡ አመልክተዋል ።

አቶ መለስ በህይወት እያሉ የትግራይ እንደስትሪ ግንባታዎችን ምን መሆን እንዳለባቸው የፃፉትን ፅሁፍ ለመተግበር በሰፊው እየተሰራ መሆኑን ወ/ሮ አመልክተዋል። ወ/ሮ አዜብ መስፍን ለዋልታ የሰጡትን ቃለምልልስ መነሻ ያደረገ ተጨማሪ ዘገባ ከዜና ቀጥሎ እናቀርባለን ።