ኢሳት (ህዳር 13 ፥ 2009)
ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝትን ያደረጉት የሞሮኮ ንጉስ በሃገሪቱ የነበራቸው ቆይታ ሞሮኮ ወደ አፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አባልነት ለመመለስ እያደረገች ላለው ጥረት የማግባባት ስራን ለማከናወን እንደነበር ተገለጠ።
ለዚሁ ዘመቻ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት በኩል የድጋፍ ቃል የተገባላቸውን ንጉስ በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካን ለመገንባት የ2.3 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት መፈራረማቸውን አፍሪካ ቢዝነስ የተሰኘ መጽሄት ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሞሮኮ ከሁለት ወር በኋላ በአዲስ አበባ በሚካሄደው ልዩ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የመሪዎች ጉባዔ ወቅት የሞሮኮ ዳግም ወደ አባልነት እንድትመለስ ሙሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ታውቋል።
የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሞሮኮ ግዛቴ ነው ለምትላት የሳሃራዊ አረብ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዕውቅና በመስጠቱ ምክንያት ሞሮኮ ከ30 አመት በፊት ከድርጅቱ መሰናበቷ ይታወሳል።
ሞሮሞ በሃገሪቱ ላይ ያላትን አቋም ሳትለውጥ በድጋሚ ወደ አፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አባልነት በድጋሚ ለመመለስ ዘመቻ እያካሄደች ሲሆን፣ ሃገሪቱ ዳግም አባል ለመሆን ሁለት ሶስተኛ የአባል ሃገራት ድጋፍ ማግኘት እንዳለባት ለመረዳት ተችሏል።
አልጀሪያ፣ ለሰሃራ ሪፐብሊክ ከፍተኛ ድጋፍን የምታደርግ ሃገር ስትሆን፣ ሞሮኮ የያዘችውን አቋም በመቃወም በሰሃራ ሪፐብሊክ የቅስቀሳ ዘመቻ በማካሄድ ላይ መሆኗ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
የሞሮኮው ንጉስ ሞሃመድ በኢትዮጵያ የነበራቸው ጉብኝት ከኢንቨስትመንት ይልቅ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ውስጥ የፖለቲካ ጥቅምን ለማግኘት ያለመ እንደሆነ እነዚሁ ተንታኞች ለመገኛኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ በድሬዳዋ ከተማ ለማቋቋም የተስማሙት የማዳበሪያ ፋብሪካ ከስድስት አመት በኋላ ስራውን ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሞሮኮ ወርልድ ኒውስ የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።
በቅርቡ የሰሃራዊት ሪፐብሊክ ተወካዮች በግብፅ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ በግብፅና በሞሮኮ መካከል ፖለቲካዊ ውዝግብ የተፈጠረ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያና ግብፅም በንጉሱ ጉብኝት ሳቢያ መነጋገሪያ ሆነው እንደሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ሪፖርትን አቅርበዋል።
የንጉሱ የአዲስ አበባ ጉብኝት ሞሮኮ በግብፅ ላይ ያላትን ቅሬታ ለማንጸባረቅ ያለመ ጭምር መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች አስታውቀዋል።