ኢሳት (ጥር 23 ፥ 2009)
የመሪዎች ጉባዔውን በአዲስ አበባ ከተማ እያካሄደ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ሞሮኮ ከ33 አመት በኋላ ህብረቱን ለመቀላቀል ያቀረበችውን ጥያቄ ተቀበለ።
ለበርካታ ሰዓታት የተካሄደን ውይይትና ክርክር ተከትሎ ከ54 የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት መካከል 39ኙ ሞሮኮ ወደ ህብረቱ እንድትቀላቀል ድምፅ መስጠታቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
በሰሜን አፍሪካ የምትገኘው ሞሮኮ ግዛቴ ናት ብላ የምትቆጣጠራት የሰሃራ በረሃ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ በቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እውቅናን በማግኘቷ ምክንያት ከአህጉራዊ ተቋሙ ራሷን አግልላ መቆየቷ ይታወሳል።
ይሁንና ሞሮኮ ባለፈው አመት የአፍሪካ ህብረትን ዳግም ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ በህብረቱ ባለስልጣናት ዘንድ ምርመራ ሲካሄድበት ቆይቶ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የመሪዎች ጉባዔ ድምፅ እንዲሰጥበት መደረጉን ለመረዳት ተችሏል።
ለሰሃራ ሪፐብሊክ ድጋፍ ተሰጣለች የምትባለው አልጀሪያ በጉባዔው ወቅት በሞሮኮ ላይ ተቃውሞን ያቀረበች ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካም ሃገሪቱ ዳግም ወደ ህብረቱ እንዳትቀላቀል ጥረት ማድረጓን ፍራንስ 24 የቴለቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
ለሰሃራ ሪፐብሊክ ነጻነት የሚታገለው የፖሊሳሪዮ ግንባር ግዛቲቱ እንደ አንድ ሃገር እውቅናን እንድታገኝ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ድምፅ እንዲካሄድ ፍላጎት ቢኖረውም በሞሮኮ ግፊት ሂደቱ አለመከናወኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይሁንና ሁለቱ አካላት ልዩነታቸውን ባልፈቱበት ሁኔታ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለሰሃራ ሪፐብሊክና ዕውቅናን ሰጥቶ ይገኛል።
በሞሮኮና በሰሃራ ሪፐብሊክ መካከል ያለው ፍጥጫ እልባትን ያላገኘ ሲሆን፣ የአፍሪካ ህብረት ችግሩን በሂደት የመፍታት ፍላጎት እንዳለው የህብረቱ ባለስልጣናት መግልጻቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ከአዲስ አበባ ዘግቧል።
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1975 እስከ 1976 አካባቢው የቅኝት ይዞታ የነበራት ስፔን ከስፍራው መውጣቷን ተከትሎ ሞሮኮ 60 በመቶ የሚሆነውን የምዕራብ ሰራሃት በመቆጣጠር የራሷ ግዛት እንደሆነች ይፋ ማድረጓን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይሁንና በ1976 መጨረሻ የፖሊሳሪዮ ግንባር የሰሃራ ግዛት ነጻ ሃገር እንደሆነች ከአልጀሪያ በማስታወቅ ለግዛቲቱ ነጻነት ሲታገል ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት ወደ 40 የሚጠጉ ሃገራት ለሰሃራ ሪፐብሊክ ዕውቅናን ቢሰጡም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግዛቲቱን እንደሃገር ሳይቀበል ቀርቷል።
በ18 ሃገራት የሰሃራዊ ኤምባሲ መኖሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአፍሪካ ህብረት መሪዎች የቻድ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሙሳ መሃማት ቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እኝደሆኑ በአብዛኛ ድምፅ መምረጡ ታውቋል።
በሰባተኛ ዙር ምርጫ ዕልባትን ያገኘው የመሪዎች የድምፅ አሰጣት ሂደት ከተጠበቀው በላይ ጊዜን ወስዶ የነበረ ሲሆን፣ በአባል ሃገራት ዘንድም መከፋፈልን ፈጥሮ እንደነበር መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የቻድ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ተሰናባቿን የህበረቱን ሊቀመንበር ዶ/ር ኒኮሳንዛ ድላሚኒ ዙማን በመተካት ህብረቱን ለቀጣዩ አራት አመታት ለማገልገል ስልጣን መረከባቸው ተመልክቷል።
ተሰናባቿ የህብረቱ ሊቀመንበር በሃገራቸው ደቡብ አፍሪካ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቅ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የመሳተፍ ዕቅድ እንዳላቸው በመነገር ላይ ሲሆን፣ ዶክተር ድላሚኒ ዙማ የቀድሞ ባለቤታቸውን ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ ይተካሎ ተብሎ ትልቅ ግምት ተሰጥቷቸዋል።
ድላሚኒ ቀጣዩ የደቡብ አፍሪካ ፐሬዚደንት ለመሆን ከወዲሁ የፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ (ANC) ፓርቲን አመራን ይይዛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ከደቡብ አፍሪካ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።