ታኀሳስ ፲፮(አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በየምርጫ ክልሉ ጽሕፈት ቤቶች ከታህሳስ 16 እስከ ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም ምዝገባ እንደሚካሄድ የሚታወቅ ቢሆንም አንድነትና መኢአድ ፓርቲዎች ከምርጫ ቦርድ ጋር ከገቡት አሰጥ አገባ ጋር ተያዞ በምርጫው የመቀጠላቸው ነገር አጠራጣሪ መሆኑ ታውቆአል፡፡
አንድነት እና መኢአድ በመጪው ምርጫ ለመወዳደር ወስነው የምርጫ ምልክት ለቦርዱ ካስገቡት ፓርቲዎች መካከል ሲሆኑ ቦርዱ ፓርቲዎቹ ያቀረቡትን ምልክት ላይ ለመወሰን ያላሟሉት የሕግ ጉዳይ አለ በሚል ሰሞኑን መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች አላሟሉም ከተባሉት መካከል አንዱ በፓርቲዎቹ ውስጥ ከተፈጠረ ውዝግብ ጋር ተያይዞ ትክክለኛ አመራሮቻቸውን አላሳወቁም ፣ የምርጫ ሕጉንና ሕገደንባቸውን አላከበሩም የሚለው የምርጫ ቦርድ ክስ ይገኝበታል፡፡ ፓርቲዎቹ ይህንን ችግር በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አስተካክለው እንዲቀርቡ ቦርዱ ታህሰስ 4 ቀን 2007 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ወስኖአል፡፡
በዚህም ውዝግብ ምክንያት ፓርቲዎቹ ለአምስት ሳምንት ገደማ በሚቆየው የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎች ምዝገባ ብቁ አይደሉም በሚል ከወዲሁ ሊሰርዛቸው ይችላል የሚል ግምት መኖሩን ምንጮቻችን ዋቢ በማድረግ የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ገልጿል፡፡ ቦርዱ በአሁኑ ሰዓት ከፓርቲዎቹ ጋር እየተጻጻፈ ያለው ደብዳቤ በኃላ ለሚወስደው እርምጃ ሕጋዊነት ለማላበስ ታቅዶ መሆኑን ምጮቻችን አስታውሰው ፓርቲዎቹ ሕግና ስርዓትን አላከበሩም በሚል ከምርጫው በማስወገድ ኢህአዴግ ከጥቂት አጃቢ ታማኝ ፓርቲዎች ጋር ለምርጫው ሊቀርብ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
ጠ/ሚኒስትር ኃ /ማርያም ደሳለኝ በምርጫ የሚፎካከሩዋቸውን ፓርቲዎች በሶስት መደቦች በመክፈልና ቀይ እና ቢጫ ካርድ የተሰጣቸው እንዳሉ በመግለጽ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ሰሞኑን ማስተላለፋቸው ኢህአዴግ ለነጻና ፍትሐዊ ምርጫ እንዳልተዘጋጀ የሚያሳይ መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጿል።
በተመሳሳይ ዜና ደግሞ ታህሳስ 12/ 2007 ዓ.ም የተካሄደው የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ “በሀገራችን የምርጫ ቦርድ አለ ወይ” እንዲል አድርጎታል በማለት አንድነት ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
የታህሳሱ 12 “የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ነፃና ገልልተኛ አልነበረም ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የምርጫ ህጉን ተከተሎ ያልተካሄደ ሌላው ይቅርና የራሱ የምርጫ ቦርድ መመሪያን እንኳን ያልተከተለ ከመሆኑ አንፃር ተካሄዷል ብለን አናምንም” ሲል ፓርቲው አስታውቋል።
ህዝቡ በምርጫ ቦርድ በእኩል በይፋ የስብሰባ ጥሪ ያልተደረገለት መሆኑ፣ ፓርቲው ባሰማረባቸው የምርጫ ጣቢያ ቦታዎች ከሞላ ጎደል በአንድ ለአምስት ስርዓቱ ካደራጃቸው የራሱ አባላትና ደጋፊዎች በስተቀር ሌላው ህዝብ ሳያውቅ የተካሄደው መሆኑ፣ ከአስር ሺዎች በላይ ነዋሪ ያለባቸው አከባቢዎች ሀምሳ እና መቶ ሰው በተገኘባቸው አዳራሾች መካሄዳቸውን በችግርነት አንስቷል።
በመላ ሀገሪቱ የምርጫውን ሂደት ለመታዘብ የተሰማሩ አባሎቻቸው በፀጥታ ኃይሎች ለእስርና ለእንግልት መዳረጋቸውን፤ በበርካታ አከባቢዎች ምንም ዓይነት ምርጫ ያልተካሄደ መሆኑ ፤ በ2002 ምርጫ ታዛቢ የነበሩ ሰዎች እንዳሉ ለዘንድሮው የ2007 ምርጫም ታዛቢ እንዲሆኑ በጅምላ እንዲፀድቅላቸው መደረጉ በተለይም በአከባቢው የሌሉና የሞቱ ሰዎችም ጭምር የህዝብ ታዛቢ ሆነው የተመረጡበት ሁኔታ መፈጠሩ በተጨማሪ ችግርነት ተገልጿል።
በዘንድሮ የሚካሄደው የ2007 ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ገለልተኛና ተኣማኒ እንደማይሆን ከወዲሁ የሚያረጋግጥ ነው የሚለው አንድነት፣ ኢህአዴግንና ምርጫ ቦርድን እያጋለጠ በህዝባዊ ንቅናቄ ህዝቡን አደራጅቶ ትግሉን በቆራጥነት ይቀጥላል ሲል መግለጫውን ደምድሟል።
በሌላ በኩል ደግሞ በደሴ ዙሪያ የሚገኙ ቀበሌዎች ህዝቡ ኢህአዴግን እንደሚመርጥ ቃል የሚገባባትን ፎርም እንዲሞላ እየተገደደ ነው። ፎርሙን ያልሞላ ከማንኛውም ጥቅም እንደሚገለል የተገለጸ ሲሆን፣ አንዴ ፎርሙን የሞላ ሰው በሁዋላ ላይ መቀየር እንደማይችል ተገልጾለታል።